ከኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማህበረሰብና የተለያዩ ሚሲዮኖች ለኮሮናቫይረስ መከላከል ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

168

 አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና ዳያስፖራ ማህበረሰብ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን የውጭ አገሮች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

ዓለምን ለሁለንተናዊ ቀውስ እየዳረገ ባለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ሉላዊ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም አገሮች የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያም በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን የተባበረ ክንድ በመሻት ብሔራዊ የኮሮናቫይረስ መከላከል የሀብት አሰባሳቢ ግብረኃይል በማቋቋም ወደ ስራ ከገባች ሰነባብታለች።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንም የተቻላቸውን እጃቸውን በመዘረጋት ላይ ሲሆኑ በውጭ የሚገኘውን ድጋፍ የሚያሰባስበው የግብረሃይሉ አንዱ ክንፍ ነው።

የውጭ አገራት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ማምሻውን ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚቴው በየክፍላተ ዓለም ከሚገኙ ሚሲዮኖችና የዳያስፖራ ማህበረሰብ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ የማሰባሰብ ተግባር ላለፉት 15 ቀናት አከናውኗል።

በዚህም ኮሚቴው በሚሲዮኖች የአደራ ሂሳብ ቁጥር፣ በባንኮች ሬሚታንስ፣ በኢትዮ ቴሌኮም ድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕላትፎርም የተዘጋጁ ሲሆን በዚህም በየአገሮች የሚገኙ 60 ሚሲዮኖች ሰራተኞችና የዳያስፖራ አባላት በገንዘብ፣ በአይነትና በሙያ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰቡ ከዚህ በፊት በተለያየ አገራዊ የልማት ስራዎችና የአደጋ ጊዜ አለኝታ ሆኖ መቆየቱን የገለጹት አምባሳደር ብርቱካን፤ ''የወቅቱን ድጋፍ ለየት የሚያደርገው ወረርሽኙ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም ዳያስፖራው ከራሱ አልፎ ወገኑን የማስቀደም ተግባር ላይ መሰማራቱ ነው'' ብለዋል።

በዚህም እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞችን ጨምሮ ከ60 ሚሲዮን ሃላፊዎችና ሰራተኞች ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በድምሩ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

ከነዚህም መካከል ከአቡዳቢ 2 ሚሊዮን፣ ከዱባይ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን፣ ከቤጂንግ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ ከካናዳ ኦታዋ 1 ሚሊዮን እንዲሁም ከስዊዘርላንድና ኦስትሪያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል።

''በዚህም በድምሩ 18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተገኘ ሲሆን ሁሉም በኮሚቴው እጅ የገባ ድጋፍ ነው'' ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮ-ቴሌኮም ባመቻቸው ኢትዮሬሚት የተሰኘ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስርዓት ከ302 ሺህ 587 ብር በላይ እንደተሰበሰበ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አባላት በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ32 ሚሊዮን የሚገመት ድጋፍ ለማሰባሰብ ከሰሞኑ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚቴው ባይረከብም በዋሽንግተን በኢንተርኔት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልት 'ጎፈንድሚ' አማካኝነት 27 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ እንደተሰበሰበ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች በአይነት ድጋፍ በሚሲዮኖች በኩል እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከፓሪስ፣ ፍራንክፈርት፣ ስዊዘርላንድ፣ ኒው ደልሂ፣ ዱባይ፣ ሎስአንጀለስ፣ ቻይና፣ ጆሀንስበርግ፣ ዋሽንግተን የተለያየ የቁሳቁስ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

ከድጋፎች መካከልም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ መድሃኒት፣ የእጅ ጓንት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የሙቀት መለኪያ መሳሪያና የሆስፒታል አልጋዎች ይገኙበታል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ ቤታቸውን መንግስት በሽታውን ለመከላከል ለማንኛውም አገልግሎት እንዲጠቀምበት የለገሱ ኢትዮጵያዊያንም መኖራቸው ተገልጿል።

ለአብነትም በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት አቶ ብሩክ ወልዴ ዓለምገና ከተማ የሚገኝ ባለ18 መኝታ ክፍል ፔንሲዮን ለግሰዋል።

የሎስአንጀለስ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታሪኩ ክፍሌና ባለቤታቸው ወይዘሮ ፍሬህይወት ጥጉ ሰበታ ከተማ የሚገኝ ህንጻ አበርክተዋል።

ጆሃንስበርግ የሚኖሩት አቶ ዳግማዊ መኮንንና ባለቤታቸው ሕይወት አየነው አዲስ አበባ የሚገኝ ሆቴል ሲለግሱ የአብሲኒያ አየር መንገድ ባለቤት አቶ ሰለሞን ግዛው ለአደጋ ጊዜ ነጻ የሄሊኮፕተር በረራ አገልግሎት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ለችግር ጊዜ ለወገናቸው ለቆሙ ኢትዮጵያዊያን ምስጋና ያቀረቡት አምባሳደር ብርቱካን፤ በየአገሮቹ ካለው የዳያስፖራ መጠን አንጻር አሁንም ድጋፉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅቱ ከማንኛውም አመለካከት በላይ መተሳሰብን በተግባር ማረጋገጥ የሚያስፈለግበት በመሆኑ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ይህን ክፉ ጊዜ በመተባበር ማለፍ አለብን ሲሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም