በሐረር ከተማ የሚገኙ የንግድ ማዕከላት ባለቤቶች የቤት ኪራይ ስረዛ አደረጉ

112

ሐረር (ኢዜአ) ሚያዚያ 1 / 2012  በሐረር ከተማ የሚገኙ የንግድ ማዕከላት ባለቤቶች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የንግድ ስራው በመቀዛቀዙ ለተከራዮቻቸው የወራት ቤት ኪራይ ስረዛ ማድረጋቸውን ተናገሩ ።ባለ ንብረቶቹ  ያደረጉት አስተያየት  ለተቀዛቀዘው ስራ እፎይታ እንደሰጣቸው ተከራይዎች ተናግረዋል።

በከተማው በህንጻ ተቋራጭ ስራ የተሰማሩትና የአውሃሂም የንግድ ማዕከል ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም መሀመድ እንደገለጹት በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አቅሜ በፈቀደ መልኩ ከክልሉ መንግስት ጋር እየሰራሁ እገኛለሁ ብሏል ።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን  የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንዳደርግ በጠየቀኝ መሰረት 100 ሺህ ብር ለግሻለው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የንግድ ስራ መቀዛቀዝ በመታየቱና ችግሩን ለመጋራት በማሰብ በንግድ ማዕከላቸው ውስጥ የሚገኙ 10 ተከራይ ነጋዴዎችን ሁለት ወራት ከኪራይ ነጻ እንዲሰሩ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኦሬንታል ትሬዲንግ የንግድ ማዕከል ባለቤት አቶ ኑሜር አብዱላዚዝ በበኩላቸው በንግድ ማዕከሉ ውስጥ 26 ግለሰቦች ተከራይተው በተለያዩ የንግድ ስራ ተሰማርተዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የንግድ ስራ መቀዛቀዙ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ነጻ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ በወር በአጠቃላይ የሚያገኙት 480 ሺህ ብር መተ  ዋቸውን ተናግረዋል።

እንደ አከራዩ ገለጻ በተለይ በክልሉ የሚገኙ ችግረኞችን ለመደገፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ እና ተከራዮችን እንዳይጨነቁ ባለሃብቱና አከራዮች  አስተያየት ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል ።

በክልሉ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ገበያ በመቀዛቀዙ 5 ሺህ ብር የወር የቤት ኪራይ  ከየት አምጥቼ እከፍላለሁ ብዬ ስጨነቅ ነበር ያሉት ደግሞ  በአው ሃኪም የገበያ ማዕከል በህንጻ መሳሪያ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሐያት እንዲሪስ ናቸው ።

የህንጻው ባለቤት  ሁለት ወር ከቤት ኪራይ ነጻ ስላደረጉልኝ እፎይታ ሰጥቶኛል ብለዋል ።

ለቤት ኪራይ በወር 4 ሺህ 600 ብር እከፍል ነበር ያሉትና በመድሃኒት ቤት የንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ እስራኤል ተሾመ እንዳሉት አሁን ካለው ወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ ኪራይ መክፈል ከብዶኝ ነበር ሆኖም ግን የህንጻው ባለቤት ለሁለት ወራት ከኪራይ ነጻ አድርጎውልናል በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በክልሉ ትናንት በተጀመረው የገቢ አሰባሰብ መክፈቻ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ በድጋፉ ስራ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው ጥሪ ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

እስከ አሁንም ከክልሉ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል።