የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲውል የተለያዩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

116

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲውል የተለያዩ ድርጅቶችና ባለኃብቶች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ። 

የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዲሁም የኮሚቴው አባል አቶ አበበ አበባየሁ ድጋፉን ተቀብለዋል።   

ቡና ላኪ ባለኃብት ሀጅ ሰኢድ ያሲን፣ ማግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ፋንቱና ቤተሰቡ ንግድና ኢንዱስትሪ ኩባንያ እና አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ እያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።        

እንዲሁም ኢትዮ ላይፍ ኢንሹራንስ 500 ሺህ ብር ድጋፍ ሲያደርግ በተመሳሳይም የአዲስ አባባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር 500 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ፍሮንትራይ የተሰኘው የጥናት ማዕከል ደግሞ 150 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።   

ሀጂ ሰኢድ ድጋፉን በሰጡበት ወቅት፤ ''መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት በተቻለ መጠን ድጋፍ አደርጋለሁ'' ብለዋል።  

''ካደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በ2 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውን ክፍሎች ያሉት ቤት ሰጥቻለሁ'' ያሉት ባለኃብቱ፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ህንጻ ተከራዮች ለአንድ ወር በነጻ እንዲሰሩ እንደፈቀዱ ገልጸዋል።

''በአገሪቷ የተከሰተውን ወረርሽኝ በመግታት ረገድ የሚሰጠውን ድጋፍ እናጠናክራለን'' ያሉት ደግሞ የናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ንጉስ አንተነህ ናቸው።

የፍሮንትራይ ጥናት ማዕከል ተወካይ አቶ አለነህ ማህጸንቱ በበኩላቸው ማዕከሉ ከሰጠው 150 ሺህ ብር ድጋፍ ባለፈ በኮሮናቫይረስ ተጽዕኖ ዙሪያ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ጥናት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።  

የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ድጋፉን ላደረጉ ድርጅቶችና ባለኃብቶች ምስጋና አቅርበዋል።  

''በሽታውን ለመመከት ከምንግዜውም በላይ አንድነታችን ሊጠናከር ይገባል'' ያሉት ሰብሳቢው፤ ''ተባብረን ይሄን ጊዜ ማለፍ አለብን'' ብለዋል።

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ድጋፉ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።  

የኮሚቴው አባል አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው ''መተጋገዝ ከተቻለ፤ አንዱ ሌላውን ማሰብ ከቻለ ችግሮችን ማለፍ እንችላለን'' ሲሉ ተደምጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ብሄር፣ ሀይማኖት፣ ፖለቲካና ጾታ ሳይገድባቸው ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አስታውሰው፤ ''ይህም የጋራ ጠላትን በጋራ ለመመከት የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አመላካች ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም