በዞኑ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ 5 ግለሰቦች ከዘጠኝ ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

64
ደብረብርሃን ዜና 25/12010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያየ ጊዜ በአሰቃቂ ሁኔታ በሰው ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ 5 ግለሰቦች ከዘጠኝ ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የፍርድ ቤቱ የወንጀል ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ትዛዙ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ወንጀለኞቹ ከባድ ቅጣት የተወሰነባቸው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 32/27539/1/ሀን እና ሌሎችንም ተላልፈው በመገኘታቸው ነው። ቅጣቱ ከተወሰነባቸው መካከል በመንዝ ቀያ ወረዳ ቀበሌ 09 በቂም በቀል ተነሳስተው በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ሕይወት ያጠፉት እምሩ ቀማው እና ደጉ ዘነብ የተባሉ ተከሳሾች ይገኙበታል። ግለሰቦቹ ጨለማን ተገን በማድረግ ሟች አትርሳው መለሰኝ የተባለን ግለሰብ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት መግደላቸው ተረጋግጧል። ተከሳሾቹ በፈፀሙት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል አንደኛ ተከሳሽ እምሩ ቀማውን በእድሜ ልክ ፅኑ እስራትና በእድሜ ልክ ከሰብአዊ መብት እንዲገደብ ሲፈረድበት። የወንጀሉ ተባባሪ በሆነው ደጉ ዘነበ ላይ ደግሞ 18 ዓመት ጽኑ እስራትና አራት ዓመት ከማህበራዊ ግንኙነት እንዲታገድ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፏል። በተመሳሳይ በስያ ደብርና ዋዩ ወረዳ ወሌ ደነባ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩትን በላቸው ቶማስንና ባለቤቱን አይናለም ቶላን በቂም በቀል ተነሳስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ በገደሉት መስፍን ነጋሽ እና ቹቹ በለጠ ላይም የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷል። በእዚህም መስፍን ነጋሽ በዕድሜ ልክ እስራትና 5 አመት ከህዝባዊ መብቱ እንዲገደብ እንዲሁም ቹቹ በለጠ የ24 ዓመት እስራትና ለ5 አመት ከህዝባዊ መብቱ በመገደብ መቀጣታቸውን አቶ ትዛዙ ገልጸዋል። በአንኮበር ወረዳ መሃል ወንዝ ቀበሌ ነዋሪ የነበረውን ሟች ታደሰ መንገሻ ሚስቴን ውሽማ ይዞብኛል በሚል ጥርጣሬ ጨለማን ተገን በማድረግ በዱላ ደብድቦ የገደለው ደርቤ ሙሉጌታ በዘጠኝ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተደርጓል። ወንጀለኞቹ በሰሩት ወንጀል እንዲከላከሉ እድል ቢሰጣቸውም የአቃቢ ህግን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ሰኔ 18 እና 19 ቀን 2010 በዋለው ችሎች ውሳኔ መስጠቱን አቶ ትዛዙ አስታውቀዋል። ወንጀለኞችን በህግ እንዲቀጡ በሚደረገው ጥረት ሃሰተኛ መስረጃዎች ተፅህኖ ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ ሕብረተሰቡ ከእንዲህ አይነት ወንጀል ራሱንና ቤተሰቡን በመጠበቅ መረጃዎች ትክክለኛ እንዲሆኑና ፍትህ እንዳይዛባ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዚህ ዓመት ብቻ በሰው መግደል የተጠረጠሩ 337 መዝገቦች የቀረቡለት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በ328 መዝገብ ላይ ውሳኔ መሰጠቱን አስተባባሪው ገልጸዋ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም