12 የመንገድ ስራ ተቋራጮች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

130

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) 12 የመንገድ ስራ ተቋራጮች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
12 የኢትዮጵያ የመንገድ ስራ ተቋራጮች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ስራ ለመደገፍ ከ15 ሚሊዮን 300ሺ ብር ለግሰዋል።

በዚሁ መሰረት ሰንሻይን፣ አለማየሁ ከተማ፣ ኤንኤች፣ ተክለብርሀን አምባዬ እንዲሁም ዮቴክ ኮንስትራክሽ እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ብር በድምሩ አስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ራማ፣ ሚልኮን፣ እንይ፣ ማርካን ኮንስትራክሽን ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር በድምሩ አራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

ፓወርኮን እና ዮን አብ ኮንስትራክሽን እያንዳንዳቸው የ500 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ራባ ኮንስትራክሽን ደግሞ የ300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።

በዛሬዉ እለትም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር  ሀብታሙ ተገኝ ከስራ ተቋራጮቹ የተደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ለብሔራዊ  የድጋፍ  አሰባሳቢ  ኮሚቴው  አስረክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የኮሚቴው የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ስራ  ተቋራጮቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የተጀመረው የድጋፍ የማሰባሰብ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ድርጅቶች አስተባባሪና የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሳሙኤል አድማሱ በበኩላቸው፤ አሁን ከተደረገው ድጋፍ ባለፈ የተቋራጮቹ ሰራተኞች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው።

ሰራተኞች አስፈላጊ የሆኑ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንዲያገኙ መደረጉን በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም