በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ለሶስት ወራት ተራዘመ

106

መቀሌ ኢዜአ ሚያዝያ 1/2012 የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ቀደም ሲል የደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ ሶስት ወራት አራዘመ።
ምክር ቤቱ አምስተኛ ዘመን ስድስተኛው አስቸኳይ ጉባኤውን ዛሬ በመቀሌ ከተማ በቪዲዮ ኮንፍረንስ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ የአዋጁን አስፈላጊነትና ይዘት ከመረመረ በኋላ ቀደም ሲል ወስኖት ከነበረው ከመጋቢት 17/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ሶስት ወራት እንዲቀጥል ወስኗል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰነድ ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦ የመራዘሙ አስፈላጊነትና በአዋጁ ከተካተቱ ድንጋጌዎች መጨመርና መቀነስ ያለባቸው ሃሳቦች ላይ ከተወያዩ በኋላ ስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ የቫይረሱ ስርጭት በተለያዩ ሀገራት ፍጥነቱን ጨምሮ በአስጊ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የክልሉን ህዝብ ከበሽታው ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲራዘም መወሰኑን ተገልጿል።

አዋጁን በሚጥሱ አካላት ላይ ከእስር ይልቅ በገንዘብ እንዲቀጡም ነው የተወሰነው።

አዋጁ የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በማይጎዳ መልኩ በማስፈጸምና እሱን ተከትሎ በተላለፈ የገበያ ክልከላ ህዝብን ከችግር ለመጠበቅ ከምክር ቤት አባላት በቀረበ ሃሳብ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ በሽታውን እየተከላከሉ ባሉበት አካባቢ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ምክር ቤቱ  አሳስቧል።

በምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርእሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "የገበያውን ችግር ለመፍታት ኮማንድ ፖስቱ ከዞኖችና ወረዳዎች ጋር በመወያየት ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ግብይት ሊካሄድ ይችላል" ብለዋል።

በአዋጁ መሰረትም ከትግራይ ክልል ውጭ በተለያዩ መንገዶች ወደ ክልሉ የሚገባ ማንኛው ሰው ለ14 ቀናት በተዘጋጁ የማቆያ ስፍራዎች እንዲቆይ እንደሚደረግም ተወስኗል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ህጋዊ አፈፃፀም የሚከታተል ሰባት አባላትን የያዘ መርማሪ ቦርድ በመሰየም ጉባኤውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም