በለይቶ ማቆያ የነበሩና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው የተረጋገጠ 554 ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቀሉ

200

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2012( ኢዜአ) በለይቶ ማቆያ የነበሩ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ግለሰቦች ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ መውጣታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ። 

በለይቶ ማቆያ ከ14 ቀናት ቆይታ በኋላ የተለቀቁት 554 ግለሰቦች በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸውም ተረጋግጧል።

ዶክተር ሊያ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የለይቶ ማቆያ የኮሮናቫይረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፋ ከሚያደርጉ የዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ ነው።

በአገሪቱም የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉም  ከውጭ የሚመጡት መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንድቀመጡ ተወስኗል ብለዋል።

ይህም ውሳኔ በሠላም ሚኒስቴር አስተባበሪነት፣  ከጤና ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከጸጥታ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጰያ የመጡ መንገደኞች በራሳቸው ወጪ በሆቴሎች ክትትል እየተደረገለቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአስገዳጅ ሁኔታ ከተለያዩ አገራት ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን በዩኑቨርሲቲዎችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመንግሥት ወጪ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የአስገዳጅ የለይቶ ማቆያው ከተጀመረ እስካሁን ድረስ አስፈላጊ ምርመራ ተድርጎላቸው 14 ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ሰዎች ከለይቶ ማቆያ መውጣታቸውን ጠቁመዋል።

የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱት ግለሰቦች ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ኅብረተሰቡ ከመድሎና ማግለል ነጻ በሆነ አኳኋን ሊቀበላቸው ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ 36 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስፈላጊው የጤና ክትትል በባለሙያዎች እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተጀመረው የ14 ቀናት የለይቶ ማቆያም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 56 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በጽኑ ህሙማን ክፍል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፤ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከ89 ሺህ አልፏል።