በምእራብ ጎንደር ክልከላውን የጣሱ 76 አሽከርካሪዎች ተቀጡ

42

ጎንደር፤ ሚያዚያ 01/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከል ግብረ-ኃይል ያወጣውን ክልከላ የጣሱ 76 የሞተር ሳይክልና ባጃጅ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ተጠሪ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ጫኔ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል ከመጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ያለመንቀሳቀስ እገዳ ተጥሏል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል ያስቀመጠውን ክልከላ ጥሰው የተገኙ አሽከርካሪዎች ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ ተሸከርካሪዎችን በፖሊስ ጣቢያ እስከማቆየት የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በከተማም ሆነ በገጠር የህዝብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የተጣለውን እገዳ በመጣስ ህዝብ ሲያጓጉዙ የተገኙ 50 የሞተር ሳክልና 26 ባለ ሦስት እግር ባጃጅ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን ነው የገለጹት።

አሽከርካሪዎቹ እንደ ጥፋት መጠናቸው ከ500 እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ የተቀጡ ሲሆን ጠቅላላ የተቀጡት የገንዘብ 47 ሺህ ብር እንደሆነም ተናግረዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው አሽከርካሪዎች ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ዳግም  በተመሳሳይ  ድርጊት ተሳትፈው ቢገኙ የቅጣት ማክበጃ ውል መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል የተቀመጠው የመንቀሳቀስ ክልከላ እስካልተነሳ ድረስ አሽከርካሪዎች ህግን መጣስ እንደሌለባቸው ጠቅሰዋል። 

የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ዋና ኢንስፔክተሩ ህብረተሰቡም ክልከላውን የሚጥሱ አካላትን በመጠቆም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል ።