ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በጫካ የሚገቡ ግለሰቦች ለአካባቢው መስፋፋት ስጋት ሆነዋል

95

መተማ ኢዜአ 01/08/2012 በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በጫካ እያቆራረጡ የሚገቡ ግለሰቦች ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡
ስጋቱን ለመቀነስ ሱዳንን በሚያዋስኑ መተማ፣ ምዕራብ አርማጭሆና ቋራ ወረዳዎች የኬላ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተብሏል ።

የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ አምሳል ጥጋቡ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ከጎረቤት ሃገር ሱዳን ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ በመተማ ዮሃንስ ኬላ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በህገ ወጥ መንገድ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በጫካ እያቆራረጡ የሚገቡ በርካታ ዜጎች ምንም አይነት ክትትል ሳይደረግባቸው ከማህበረሰቡ ጋር እየተቀላቀሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ይህም ድንገት ቫይረሱ ያለበት አንድ ሰው ቢገኝ ሳይታወቅ ለበርካታ ሰዎች ሊያስተላልፍ ሰለሚችል ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

ኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ ወደ ተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ቦታ በማስገባት የመለየት ስራ እንዲሰራ አቶ አምሳል ጠይቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከላከል ኮማንድ ፖስቱ በማይደርስባቸው ቦታዎች በጫካ በኩል የሚወጡና የሚገቡ ግለሰቦች መኖራቸው ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት ስጋት እንደፈጠረባቸው የገለፁት ደግሞ የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ነጋ ሰጠኝ ናቸው።

አሁንም ድረስ በጫካ በኩል የሚደረግ የአልባሳትና የምግብ ዘይት የኮንትሮባንድ ስራ አለመቆሙን ጠቅሰው ለበሽታው መስፋፋት አይነተኛ ምክንያት እንዳይሆን እሰጋለሁ ብለዋል።

በቋራ ወረዳ የገለጉ ከተማ ነዋሪ አቶ አያናው ጥላሁን በበኩላቸው በወረዳው የለይቶ ማቆያ ካለመዘጋጀቱ ባለፈ የሚደረገው የኬላ ቁጥጥር በተለመደው መግቢያና መውጫ በር ብቻ እየተከናወነ ይገኛል።

የኮሮና ቫይረስ ይኑርባቸው አይኑርባቸው ያልተረጋገጡና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥጥር አነስተኛ መሆን የህይዎት ዋጋ እንዳያስከፍል ከወዲሁ ጥብቅ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የዞኑ ሰላምና ህዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደገለፁት የፀጥታ አካላት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረጉ ነው ብለዋል ፡፡

ይሁን እንጂ ዞኑ ከሱዳን ጋር የሚዋሰንበት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም በመሆኑ  ህዝቡ የራሱንና የቤተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ በሱዳን ቆይተው የሚገቡ ግለሰቦች በተዘጋጀው መለያ ቦታ እንዲቆዩ ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል ።

ኮሮና ቫይረስ የህዝቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ከሌላ ቦታ የሚመጡ ግለሰቦችን በመጠቆም አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ህብተረሰቡ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።

የዞኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከል ግብረ-ኃይል ፀሃፊና የማህበራዊ ልማት መምሪያ ሃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ እንዳሉት በአብርሃጅራና ገንዳ ውሃ ከተሞች የለይቶ ማቆያ ተዘጋጀቶ እየተሰራ ነው።

በለይቶ ማቆያውም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ሁለት ሳምንታትም 200 የሚሆኑ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዜጎች በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።

ግብረ ኃይሉ በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሚገቡ ግለሰቦችን ህብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በማድረስ ወደ ለይቶ ማቆያ ክፍል እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም