በኮሮና ቫይረስ ሳይዘናጉ ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ…የያቤሎ ከተማ ነዋሪዎች

56

ነገሌ ኢዜአ ሚያዝያ 1/2012  በኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳይዘናጉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናከረው እንደሚቀጥሉ የቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ገነት በቀሉ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን በመከላከል ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ።

ማህበራዊ ርቀታችንን እየጠበቅን የጤና ስጋቱን በመከላከል የህዳሴውን ግድብ ሰርተን በማጠናቀቅ አንድነታችንን ፣ ትብብራችንንና ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን ብለዋል ።

ባለፉት አመታት ለግድቡ ግንባታ በሁለት ዙር የገዙትን የ3 ሺህ ብር ቦንድ በማስታወስ በወቅታዊ የጤና ስጋት ለህዳሴው ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዳይስተጋጎል ድጋፉንና መከላከሉን ጎን ለጎን እንዲካሔዱ መስራት አለብን የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ በሀይሉ አድማሱ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በውጭ ጫና ፣ ጣልቃ ገብነትና በኮሮና ቫይረስ ስጋት እንዳይደናቀፍ እንረባረባለን ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት ማህበራዊ ርቀታችንና ንጽህናችንን ጠብቀን የጤና ስጋቱን በመከላከል ግድቡን ሰርተን በማጠናቀቅ የመተባበር አኩሪ ተግባር ልንፈፅም እንደሚገባ ገልፀዋል ።

ቀደም ባሉት አመታት ከገዙት የ2 ሺህ 300 ብር ቦንድ በተጨማሪ 8100 ኤ ብለው ገንዘብ በመላክ የሚያደርጉትን ድጋፍ እስካሁን እንዳላቋረጡ ተናግረዋል ።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ  በገንዘብም ሆነ በአይነት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በግል ፍላጎትና ተነሳሽነት የማደርገውን ድጋፍ እቀጥልበታለሁ ብለዋል፡፡

የያቤሎ ከተማ ነዋሪ አቶ ጎዳና ጎሎ እንዳሉት ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ስጋት ያለ ቢሆንም የጤና ችግሩን በመከላከል የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል  የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በጋራ መረባረብ አለብን የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ።