የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው

155

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህልወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ "የዓለም ጤና ድርጅት በዋነኛነት በአሜሪካ ቢደጎምም፤ ለቻይና የወገነ ድርጅት ነው" ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

አሜሪካ ለድርጅቱ የምታደርገውን ድጋፍ  ለማቆም እንደምትችልም ፕሬዚዳንቱ ማስፈራሪያ የሚመስል መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህንን ተከትሎም ዶክተር ቴድሮስ ትናንት በሰጡት መግለጫ " ኮሮናቫይረስን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የለብንም " ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አጋዥና አጋር አካላት ለድርጅቱ ለሚያደርጉት ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሆኖም ዶክተር ቴድሮስ በዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊነታቸው የግድያ ዛቻ እንዲሁም የዘረኝነት ጥቃቶች የተሰነዘረባቸው መሆኑን አልደበቁም።

"በጥቁርነቴ እኮራለሁ፤ የግድያ ዛቻውም ግድ አይሰጠኝም " ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በመሆኑም በአሜሪካ በኩል በዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊ ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ትችትና ተቃውሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች አውግዘውታል።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ፣ የናሚቢያው ፕሬዘዳንት ሀጌ ጄኒግቦ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሳ ፋኪ ማሐማት ለዶክተር ቴድሮስ ድጋፋቸው ከገለጹ መሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።  

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ “አሁን በዓለም ላይ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሰዎችን ህይወት ማዳን ነው ” ብለዋል።  

በዶክተር ቴድሮስ አመራር ሰጪነት የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅትም በአስፈላጊው ወቅት የተሰጠውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ እየተወጣ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡   

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነው፤ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን አካላት መጠበቅ እና መደገፍ ይጠበቅብናል ሲሉም ገልፀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሳ ፋኪ ማሐማት "ከዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ጎን ነኝ" ማለታቸው ይታወሳል።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜም ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ገልፀው ከዶክተር ቴድሮስ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እና የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አመራር የተለየ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም፥ “የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አመራርነት በምንም የማይተመን ነው” ብለዋል።

የናሚቢያው ፕሬዘዳንት ሀጌ ጄኒግቦ በበኩላቸው "የመላው ዓለም ትብብር አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት አብሮነትን ያሳዩ እውነተኛ መሪ" ሲሉ ዶክተር ቴድሮስን ገልጸዋቸዋል።   

የናይጄሪያ መንግስትም ለዓለም ጤና ድርጅት እና ለዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሙሉ ድጋፉን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም