የደባርቅና ደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ድጋፍ አደረጉ

62

ጎንደር/ደብረ ብርሃን ሚያዚያ01/2012- የደባርቅና የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ ።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ስምንት የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን በሰሜን ጎንደር ዞን ለሚገኙ  ሁለት ሆስፒታሉችና ስድስት ጤና ጣቢያዎች አስረክቧል።

በተመሳሳይ መልኩርቀት ላይ ለሚገኙና የትራንስፖርት እጥረት ላለባቸው ስምንት የገጠር ጤና ተቋማት በቅርቡ የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በማስመጣት ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናገረዋል።

በተጨማሪምበጤና ተቋማቱ ተመድበው ለሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ግላብ፣ የፊት ማስክና የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማቅረብ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመታደግ ድጋፍ ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅትም 68 አልጋዎች የያዙ የተማሪዎች የማደሪያ ክፍሎች ከኮሮና በሽታ ጋር በተያያዘ ለለይቶ ማቆያ ዝግጁ ማድረጉንና የተሟላ የምግብ አገልግሎት በዩቨርሲቲው እንደሚቀርብ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡   

በተያያዘ ዜና የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ከ12 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና የሽንት ቤት ማጽጃ ፈሳሽ ሳሙና ማስረከቡን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር አልማዝ አፈራ  እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ የጤና ተቋማት ነው።

ከድጋፉ  ውስጥም ሰባት ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር ሲሆን  ከአምስት ሺህ ሊትር በላይ ደግሞ የመፀዳጃ ቤት ፈሳሽ ሳሙና ነው ተብሏል ።

ሳንታይዘሩ በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኬሚካል እንጂነሪንግና  ከባዮ ሜዲካል ጋር በመቀናጀት የተመረተ ሲሆን ፈሳሽ ሳሙናው ደግሞ  በአንኮበር የመድሀኒት እጽዋት ቅመማ ፕሮጀክት የተመረተ ነው።

የሰሜን ሸዋ ዞን  ጤና መምሪያ ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ያደረገው ድጋፍ በዞኑ ውስጥ ለሚገኙ 10 ሆስፒታሎችና 98 ጤና ጣቢያዎች የሚሰራጭ ነው ብለዋል።

ሌሎች ባለሀብቶችም የዩኒቨርሲቲውን ፈለግ በመከተል ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ወይዘሮ ፀዳለ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም