የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኮማንድ ፖስት ሳይሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚተዳደር መንግስት አስታወቀ

1239

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኮማንድ ፖስት ሳይሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚተዳደር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ህብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገርንና ህዝብን ለመጠበቅ ተብሎ የወጣ መሆኑን ተረድቶ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና በህዝብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኮማንድ ፖስት አይተዳደርም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስተዳድረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የሚኒስትሮች ኮሚቴ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ እንዲሆን የተደረገው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ተጥሎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ‘ኮማንድ ፖስት’ የሚለው የአስተዳደር ስያሜ የፈጠረውን አሉታዊ ስሜት ለማስወገድ በማለም እንደሆነ አመልክተዋል።

”የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ኮማንድ ፖስት ሲባል ህዝቡ ላይ የተፈጠረ መጥፎ የስነ ልቦና ተጽዕኖ አለ” ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈጸም ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል የአስተዳደር መንገድ መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አዋጁን በብቃት በማስፈጸም የህዝቡን ጤንነት ለማስጠበቅና የመጣውን አደጋ ለመቀነስ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ አካላትን በአባልነት የያዘ ኮሚቴ ሊቋቋም እንደሚችል አመልክተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው ህዝቡን ለመታደግ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባ የገለጹት ወይዘሮ አዳነች፤ ህዝቡ ‘የእኔ አዋጅ ነው’ በሚል ወስዶት ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።

”አገራችንን ከዚህ አፍጥጦ ከመጣብን ቀውስ ሊያወጣ የሚችል ርምጃ ነው የሚወሰደው” ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ፤ አዋጁ ማንኛውም አካል ላይ በተለየ ሁኔታ ጉዳት የማያደርስና ተጽዕኖ የማያስከትል መሆኑን አብራርተዋል።

አዋጁን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ በየጊዜው እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

ህዝቡ ራሱን ከበሽታው ለመከላክል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡ ሲሆን የሚያደርገውን ትብብርና ጥንቃቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ በንቃት እንዲያከናውንም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ትናንት ማብራሪያ መስጠቱ ይታወቃል።