በድሬዳዋና በሰሜን ሸዋ ዞን ለኮሮና መከላከል 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ተለገሰ

78

ድሬዳዋ/ ፍቼ / ሚያዚያ 01/2012 ዓም በድሬዳዋና በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ከባለሃብቶችና ከህብረተሰቡ 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊና የኮሮና ቫይረስ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሱልጣን አልይ ለኢዜአ እንደገለፁት ቫይረሱ በችግረኛ ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመመከትና ለመቀነስ ድጋፍ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡

የድጋፍ አሰባሰቡ ወጥና የተሟላ እንዲሆን ከቀበሌ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በእስከ አሁኑ ጥረት ባለሃብቶችና ድርጅቶች በገንዘብና በዓይነት 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጋቸውን ገልፀዋል ።

በተለይ አንዳንድ ሰዎች ያላቸውን መኖሪያና መስሪያ ቦታ ሳይቀር ለለይቶ ማቆያ ፣መከታተያነት ለጤና ባለሙያዎች መኖሪያ እንዲውል የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

አቶ አቤል ከበደ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት የሚያሰበሰበው ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትልና ችግረኞችን ለማገዝ ወሳኝ በመሆኑ ቅስቀሳው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የተለየያዩ የሀብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚውል የ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የገንዘብና ቁሣቁስ ድጋፍ አበርክተዋል ።

የዞኑ አስተዳዳሪ የካቢኔ ጉዳዮች ምክር ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው አክሊሉ እንደገለጹት ባለፉት አስር ቀናት የተገኘው የቁሣቁስና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ በዞኑ 13 ወረዳ ከሚገኙ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች፣ ማህበራትና ከዞኑ ሥራ አስፈፃሚ አባላት የተበረከተ ነው ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተሰበሰበው ድጋፍ ውስጥ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ለምግብና ለንፀህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሦች ሲሆን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ደግሞ በጥሬ ገንዘብ የተሰጠ መሆኑን አቶ ጋሻው ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም