ኢትዮጵያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ የሚያግዝ የ600 ሺህ ዶላር ድጋፍ አገኘች

863

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ ላሰበችው “የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን” መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የሚያግዝ የ600 ሺህ ዶላር ድጋፍ አገኘች። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ጋር ገንዘቡ ጥቅም ላይ በሚውልበት ሁኔታ ላይ ከተወያዩ በኋላ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የዲጂታል ሂደቱ አጠቃላይ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማቃለል የጎላ ሚና አለው ይላሉ ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ።

የ’ዲጂታላይዜሽን’ ሂደቱ በዚህ ወቅት ዓለምን እየመራት መሆኑን ገልጸው ሂደቱ ገበያን ለማቀላጠፍ፣ ትምህርትን እና ህክምናን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ያዘምናል ብለዋል።

በመሆኑም ሂደቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረጉ መንግስት የበለጠ ለዜጎች እንዲቀርብ የሚያደርግ ሲሆን ዜጎች ቤት ሆነው አገልግሎት የሚሰጡበትና ግልጋሎት የሚያገኙበትን ዕድልም ይፈጥራል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት ‘ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን’ የኢትዮጵያ ቢሮ ትግብራውን በእውቀትና በክህሎት ለመደገፍ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።

ድርጅቱ የስትራቴጂውን ዝግጅትም በቅርበት በክህሎትና በሰው ሃይል ሲደግፍ መቆየቱንም አቶ ሲሳይ ገልፀጸዋል። 

በዚህ ወቅትም ከድርጅቱ በኩል የሚደረገው ድጋፍም የቴክኒክ ስራውን የሚያግዝና ሙያተኛን የመቅጠር ስራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ወጭው እስከ 620 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ሲሆን ስትራቴጂውም በጥቂት ጊዜ ውስጥ በመንግስት ጸድቆ ወደ ትግበራ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም ድርጅቱ ከፍተኛ እውቀትና ዓለም ዓቀፍ ልምድ ያላቸውን ሙያተኞች በመቅጠር ስትራቴጂውን በአግባቡ ለመተግበር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ደኤታው አገላለፅ ይህ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የስራ ዕድል የሚያገኙ ይሆናል።

በቀጣይም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከውጪ ከሚመጡት ሙያተኞች አስፈላጊውን ልምድ እንዲቀስም የሚያግዘው መሆኑ ተገልጿል።

ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በመላው አፍሪካ በአምስት ዓመት ለ30 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ ሲሆን ኢትዮጵያም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ ነች።