የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ18ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

114

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 18ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የምክር ቤቱ ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የተወያየው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው ረቂቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነው። ኮቪድ-19 ክትባትም ሆነ መድኃኒት የሌለው፣ በፍጥነት የሚዛመት እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን በመገንዘብ፤ የቫይረሱ ስርጭት በተለያዩ ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያጠቃ እና ለብዙ ሺዎች መሞትም ምክንያት መሆኑ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር በተለመደው የጤና አጠባበቅ ዘዴ እና አካሄድ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አዳጋች በመሆኑ፤ በሃገራችን ተጨባች ሁኔታም የቫይረሱ ስርጭት እና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን እያስከተለ የሚገኝ ሲሆን ለነዚህ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኗል።

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል ሥርዓት በአንቀጽ 93 ተደንግጓል።

በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ ከሚሆኑ ሁኔታዎች አንዱ “የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት” መሆኑም ሰፍሯል።

የኮቪድ-19 የሕዝብን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ከመሆኑም በላይ የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረርሽ መሆኑን ማወጁን ተከትሎ ከ70 የማያንሱ አገሮች ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ህዝቦቻቸውን ለመታደግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥተዋል።

በአገር ደረጃ ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ሲባል ከተለመደው አሠራር ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል።

ምክር ቤቱን በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ጥቂት ማስተካከያዎችን በማከል ከዛሬ 29/07/2012 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለበት ወቅት በመሆኑ በህገመንግስቱ አንቀጽ 93 (2(ሀ)) መሰረት በአስቸኳይ ለምክር ቤቱ እንዲላክ ጭምር ተወስኗል።

 2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ ልማት ማህበር ጋር የተደረጉ 3 የብድር ስምምነቶች ላይ ነው። የመጀመሪው ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ41 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ለአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ክፍለ አህጉራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ54 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ነው።

ሦስተኛው ለሁለተኛው የኢትዮጵያ የዕድገት እና የተወዳዳሪነት የልማት ፖሊሲ ፋይናንስ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 136 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፤ ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች 0 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የእፎይታ ጊዜ ያላቸው እና በረጅም ጊዜ ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆናቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትሉት ጫና የሌለ መሆኑን እና የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚደረገው አገራዊ ርብርብ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሙሉ ድምጽ አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም