ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከቻይና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ጋር በቅርበት እየሰራች ነው

90

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽን ለመግታት የባህል ሕክምናን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር አጣምሮ ለመጠቀም ኢትዮጵያ ከቻይና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ጋር እየሰራች መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ እየተሞከረ ያለው የባህል መድሃኒትን ከዘመናዊው ጋር አጣምሮ ፈዋሽ የማድረግ ሙከራም ተስፋ ሰጪ መሆኑም ጠቁሟል።

 በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በቤጂንግ የቻይና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ተደርጓል።

ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቻይና የባህል ህክምና ለኮቪድ-19 መከላከል በአግባቡ ተጠቅማለች።

''ይህንኑ ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጥረት በቻይና ልምድ ታስደግፈዋለች'' ብለዋል።

ቻይና በሽታውን ለመቆጣጠር በዚህ ወቅት ዓለምን እያስተማረች በመሆኑ ኢትዮጵያም የረጅም ዓመት የባህል መድሃኒት የመጠቀም ልምድ ስላላት ይህንኑ መንገድ ለመከተልም መታሰቡን ገልጸዋል።

''በዚህም በአጭር ጊዜ በሽታውን ለመዋጋት በተግባር የተደገፈ ልምዳቸው ተወስዶ ተግባራዊ ይደረጋል'' ብለዋል።

የተጠቀሙባቸው የባህል መድሃኒቶች እዚህ አገር መኖራቸው ከተረጋገጠ በኋላ ጥቅም ላይ ለማዋልም ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።

በዚሁ ዘርፍ የተጀመረውንም ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከቻይናውያኑ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ሕብረተሰቡ የጤና ሙያተኞችና መንግስት ከሚጠቁማቸው የመፍትሄ አማራጭ ውጪ መጠቀም እንደሌለበትም ዶክተር አብርሃም አሳስበዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የጤና ሚኒስትሯ አማካሪ ዶክተር ሰለሞን ወርቁ እንደሚሉት፤ በውይይቱ ጠቃሚ እውቀት ተገኝቷል።

የቻይና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በሽታውን ለመከላከል የተጓዙባቸውን መንገድ የሚያሳዩ አራት ያህል ጥናቶችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይም በባህል መድሃኒቶቹ ቫይረሱ የከፋ ደረጃ ያልደረሰባቸውን ታማሚዎች በተሻለ መንገድ ማከም መቻሉንም መረዳታቸውን ያብራራሉ።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የአምባሳደሩ የኢኮኖሚና የንግድ አማካሪ ሊዉ ዩ በበኩላቸው ''ቻይና የባህል መድሃኒቶች ህክምና በመስጠት ውጤታማ ሆናለች'' ሲሉ ያረጋግጣሉ።

በመሆኑም በቻይና የተገኘው ልምድ በኢትዮጵያም ቫይረሱ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ቻይና የቅርብ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም