የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በእቃ ጭነት አገልግሎት ላይ ማሻሻያ አድርጓል - አቶ ተወልደ ገብረማርያም

147

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ጋር በተያያዘ በሚሰጠው የእቃ ጭነት አገልግሎት ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አስታወቁ።

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በመጋቢት ወር ከ45 ሺህ ቶን የእቃ ጭነት (ካርጎ) አገልግሎት መስጠቱንም አየር መንገዱ አመልክቷል።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የእቃ ጭነትና የሎጂስቲክ አገልግሎቱን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ከተቀየረው የአየር የእቃ ጭነት አገልግሎት ዓለም አቀፍ ፍላጎት ጋር እያጣጣመ እንደሆነ ገልጿል።

ለዓለም አቀፍ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አየር መንገዱ በዓለም ደረጃ ያለውን የእቃ ጭነት አገልግሎት ተደራሽነት ወደ 74 አገሮች ማድረሱን ገልጿል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የህክምና አቅርቦቶችን መደበኛ ባልሆኑ በረራዎች ለዓለም አገሮች እያሰራጨ እንደሆነም አመልክቷል።

የአየር መንገዱ የእቃ ማመላለሻ ካርጎ አውሮፕላን በፈረንጆች መጋቢት ወር ብቻ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በረራ በማድረግ 45 ሺህ 848 ቶን የእቃ ጭነት (ካርጎ) አገልግሎት መስጠቱንም ነው አየር መንገዱ ያስታወቀው።

የጭነት እቃዎቹ መድሐኒቶች፣ የህክምና አቅርቦቶችና ለጤና ክብካቤ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች ሲሆኑ በቦይንግ B777 እቃ ጫኝ አውሮፕላኖች 86 መደበኛ ያልሆኑ በረራዎች በማድረግ እቃዎቹ ተጓጉዘዋል።

''ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ በፍጥነትና በቀላሉ ለውጥ ማድረግ ከኛ የተፎካካሪነትና የተወዳዳሪነት ብቃት ከሚያሳዩ ጉዳዮች አንዱ ነው'' ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ አየር መንገዱ የእቃ ጭነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ እና ትስስሮቹ ላይ  ማሻሻያ እንዳደረገ ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ከእቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በተጨማሪ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን በመጠቀም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ በረራዎች የህክምና አቅርቦቶችን ማከፋፋሉን አመልክተዋል።

''አየር መንገዱ በበረራው ዓለም ከፈታኝና አሳዛኝ ሁኔታ ጋር እየተጋፈጠ በሚገኝበት ወቅት የህክምና አቅርቦቶችን በማጣት የሚሞተውን ሰው ቁጥር ለመቀነስና አቅርቦቱ በተለይም በጣም እርዳታው ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲደርስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው'' ብለዋል።

በዚህም አየር መንገዱ ከፍተኛ ኩራትና ክብር እንደሚሰማው በመግለጽ።

ዓለም ከየትኛውም ጊዜ በላይ የአየር የእቃ ጭነት አገልግሎት በሚፈልግበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት 24 ሰአት ያለማቋረጥ አገልግሎት ለሚሰጡት ለአየር መንገዱ የእቃ ጭነትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ክፍል ሰራተኞች ዋና ስራ አስፈጻሚው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ጃክ ማ የአፍሪካ አገሮችን ለመደገፍ ያበረከቱት ቁሳቁስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ለአፍሪካ አገሮች መከፋፈሉን አየር መንገዱ በመግለጫው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም