ከ 3 ሺህ በላይ አረጋዊያን ከጎዳና ላይ ሊነሱ ነው

118

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ 3 ሺህ በላይ አረጋዊያን ከጎዳና ላይ ለማንሳት ከአራት ድርጅቶች ጋር ተፈራረመ።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አረጋዊያንን ለመቀበል ከተስማሙ መቄዶኒያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል፣ ክብረ አረጋዊያን፣ መቅድም ኢትዮጵያና ሴዴቂያስ ማዕከላት ጋር ተፈራርመዋል።  

ሚኒስቴሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሴፍትኔት መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።   

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በ11 ከተሞች ኑሯቸውን ጎዳና ላይ የመሰረቱ 22 ሺህ ህጻናት፣ ልጅ የያዙ እናቶች፣ ወጣቶችና አረጋዊያንን መልሶ ለማቋቋም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ እየተደረሰ ነው።   

በዚህም መሰረት ከ6 ሺህ 200 በላይ ህጻናትን ከጎዳና ላይ ለማንሳት ሚኒስቴሩ ከ27 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ስምምነት መፈራረሙን ገልጸው፤ ''መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ጋምቤላ፣ ሀረር፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ያሉ ተቋማት እያነሱ ነው'' ብለዋል።እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም በትንሹ አንድ ልጅ የያዙ 1 ሺህ 380 ሴቶች በተለያዩ አገሪቷ ክፍል የሚገኙ ማዕከላት አማካኝነት የሚነሱ ሲሆን 842 ወጣቶችም እንዲቋቋሙ ይደረጋል።

ከ5 ሺህ በላይ የሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ዶክተር ኤርጎጌ ተናግረዋል።በአገሪቷ የኮሮናቫይረስን መከሰት ተከትሎ ተጋላጭ የኀብረተሰብ ክፍሎችን የማንሳት ስራው በጥንቃቄ እየተካሄደ እንደሆነም አብራርተዋል።  

የመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ በበኩሉ ''አረጋዊያንን ለመርዳት ተግባራዊ ምላሽ መስጠት መጀመሩ የሚያስደስትና ትልቅ እርምጃ ነው'' ብሏል።  

''ልማት ማለት መንገዶችና ሌሎች ግንባታዎችን ማካሄድ ብቻ አይደለም፤ ሰዎች ላይ መሥራት ትኩረት ሲሰጠው ይገባል'' ሲል ያመለክታል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም