የቤተክርስቲያኗ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት በሕፃናት መርጃ ማዕከላት ኮሮናን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገለጸ

103

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት በ36 ማዕከላት የሚገኙ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ድርጅቱ ምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት እንደገጠመውም ገልጿል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በአገሪቱ ባሉት 36 የህጻናት መርጃ ማዕከላት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ27 ሺህ በላይ አሳዳጊ ላጡ ህፃናትና ችግረኛ ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ድርጅቱ በየማዕከላቱ የሚገኙ ሕፃናትን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም ድርጅቱ በሚያስተዳድራቸው ማዕከላት ያሉ ህፃናት ከአካላዊ ንክኪ ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱና ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለህፃናቱ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ ከበሽታው  ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ቀሲስ ሳምሶን እንዳሉት፤ ለህጻናቱ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ የሚውል ሳኒታይዘር እንዲሁም የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በማዕከላቱ ያሉ ህጻናትን በተገቢው መንገድ መደገፍ እንዲቻልና አሳዳጊ የሌላቸው ተጨማሪ ሕፃናትን ወደማዕከል ለማስገባት ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

ድርጅቱ አሳዳጊ የሌላቸው ህጻናትን ከመደገፍ ባለፈ ችግረኛ ቤተሰቦች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ የገንዘብ፣ የትምህርትና የስልጠና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ቀሲስ ሳምሶን ገልጸዋል።ቀሲስ ሳምሶን እንዳሉት፤ ድርጅቱ አሳድጎ ለቁም ነገር ያበቃቸው ሕጻናት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ከተመሰረተ 46 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በእነዚህ ዓመታት ከ42 ሺህ በላይ አሳዳጊ የሌላቸው ህፃናትን አስተምሮ ለቁም ነገር ማብቃቱን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡