የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋቢት ወር 3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት አገበያየ

155

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋቢት ወር 3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 75 ሺህ ቶን የሚጠጋ ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው በኮሮናቫይረስ የተነሳ የግብይት ስርአቱ እንዳይቋረጥ መከላከል ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋቢት ወር 2012 ዓ/ም በነበሩት 21 የግብይት ቀናት 29 ሺህ 748 ቶን ቡና፣ 25 ሺህ 691 ቶን ሰሊጥ፣ 8 ሺህ 122 ቶን አኩሪ አተር፣ 7 ሺህ 338 ቶን ነጭና ቀይ ቦለቄ እንዲሁም 4 ሺህ 14 ቶን አረንጓዴ ማሾ አገበያይቷል።

በጠቅላላው በወሩ የግብይት ቀናት 74 ሺህ 950 ቶን ምርት በ3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ነው ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያስታወቀው፡፡

በዚህም ቡና 63 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብና 40 በመቶ የግብይት መጠን በመያዝ ከተገበያዩት ምርቶች ቀዳሚውን ቦታ ይዟል፡፡

ከየካቲት ወር ጋር ሲነፃፀርም የቡና ግብይት 17 በመቶ የግብይት መጠንና 5 በመቶ የግብይት ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር  ሲነጻጸር መጠኑ ሁለት በመቶ ቢቀንስም ዋጋው 24 በመቶ መጨመሩን አመልክቷል፡፡

በዚሁ ወር 25 ሺህ 691 ቶን ሰሊጥ ለግብይት ቀርቦ በ1 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡

ነጭ የሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ 71 በመቶ በመጠን እና 73 በመቶ የግብይት ዋጋ በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፡፡

አጠቃላዩ የሰሊጥ ግብይት ከቀደመው ወር በመጠን 28 በመቶ የተመዘገበ ሲሆን በዋጋ ደግሞ 30 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 8 ሺህ 122 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ97 ነጥብ 14 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡

የጎጃም አኩሪ አተር በመጠንና በዋጋ በተመሳሳይ 77 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡

እንዲሁም 7 ሺህ 338 ቶን ነጭና ቀይ ቦለቄ በ155 ነጥብ 95 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ቢሆንም ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በመጠንም በዋጋም ቅናሽ መታየቱን በመግለጫው ተመልክቷል።

የቦለቄ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 17 በመቶ የግብይት መጠን እና 44 በመቶ ደግሞ የግብይት ዋጋ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡

የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በሆነው በዘመናዊ የግብይት ስርዓቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በዋና መስሪያ ቤት እና በሁሉም ቅርንጫፎች ላይ ሠራተኞችንና ተገበያዮችን በማሳተፍ የመከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

ለዚህም አብዛኛው ግብይት በሚፈፀምበት የኤሌክትሮኒክ የግብይት መድረክ ተገበያዮችን በፈረቃ ከመመደብ ባለፈ በቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።

በተጨማሪም የቫይረሱን ስርጭት የመከላከያ መንገዶች በሚገባ ተግባራዊ እንዲሆኑ በመከታተል እና ተገበያዮች የሚቆዩባቸውን ቦታዎች በማስፋት በቂ አየር እንዲዘዋወር በማድረግ ግብይቱና አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም