የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልዝግጁ መሆናቸውን የጤና ባለሞያዎች አስታወቁ

153

አክሱም፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) ሙያዊ ሃላፊነትታቸውና ግደታቸውን በመወጣት በኮሮና ቫይረስ ለሚታመሙ ዜጎች ተገቢውን የህክምና እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ገለጸ።

የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ አስፈላጊው እገዛና የህክምና እርዳታ የሚሰጥባቸው ሶስት ሆስፒታሎች ዝግጁ መደረጋቸው ተገልጿል ።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም ዶክተር በረከት አረጋይ ለኢዜአ እንደገለጹት  የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ምክንያት ለሚያጋጥም ማንኛውንም የጤና ችግር አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ  ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።

የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልገው ሰው ፈጥኖ መድረስና አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ሙያዊ ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

 ባለሙያዎቹ ለወገኖቻቸው ሙሉ አገልገሎት ለመስጠትና መስዋእት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡም ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ የጤና ባለሞያዎችን የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የራሱና የህክምና ባለሞያዎች ህይወት መታደግ እንደሚገበው አሳስበዋል።

በሆስፒታሉ የአለም ጤና ድርጅት መስፈርት ያሟሉ ለዘጠኝ ባለሙያዎች ብቻ የሚበቃ የህክምና ቁሳቁስ  መቅረቡን ጠቅሰው በቀጣይ የበሽታውን ሁኔታ በማየት በፍጥነት አቅርቦቱ ሊሟላ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሪፈራል ሆስፒታሉ  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደጀን ገብረጊዮርግስ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ከክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር ሆስፒታሉ የኮሮና ቫይረስ የህክምና ማዕከል ሆኖ ማገልገል የሚችልበት ሙሉ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ  250 አልጋዎች፣  አምስት የቬንትሌተር ማሽንና አራት ኦክሰጅን እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።

ለለይቶ ማቆያና ለኳራንታይን የሚገቡ ሰዎች የሚቆዩበት የዩኒቨርሲቲው ዋና ጊቢ ጨምሮ ፣በዓድዋ፣ሽረና ሁመራ ሆስፒታሎች  2 ሺህ አልጋዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የሪፈራል የሆስፒታሉ ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ለመዋጋትና አስፈላጊውን የህክምና  አገልግሎት ለመስጠት ቃል መግባታችውን ገልጸዋል።

ነርስ ትርሓስ ተስፋሁነኝ በበኩሏ ያለ ምንም ፍርሃት ሙያዊ ግዴታዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆንዋል ተናግራለች ።

''የተማርነው ህዝብ ለማገልገል በመሆኑ ሙያዊ ሃላፊነታችን ለመወጣት ዝግጁ ነን''' ስትል ቀርጠኝነቷን ገልፃለች ።

የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት አልባሳት እና የህክምና መሳሪያ እጥረት  በመኖሩ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲው ኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል እና የሆስፒታሉ ላብራቶሪ ክፍል በጋራ በመሆን በቀን 100 ሊትር ሳኒታይዘር ማምረት መጀመራችውና አንዳንድ እጥረቶች በራሳቸው ጥረት እየፈቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሰቀቁስ እና የህክምና መሳሪያ ከጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል በየደረጃው ለሟሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የህሙማን ማከምና እንክብካቤ ተተኪ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ጠዓመ አርዓዶም ናቸው።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ዓዲግራት አጠቃላይ ሆስፒታል እና የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲሆኑ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ቨንቲሌተር፣የኦክሰጅን እና ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት አልባሳት እና የህክምና መሳሪያ ወደ ሆስፒታሎቹ መላካቸውን ገልጸዋል።።

የአለም የጤና ድርጅት መስፈርት ያሟሉ 370 ሺህ ጭምብል እና 312 ሰርጂካል ግላቭ መከፋፈሉን ተናግረዋል ።

በክልሉ 700 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ዙሪያ ስልጠና ወስደው ለህክምና እርዳታ ዝግጁ መደረጉን የስራ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም