የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ህክምና ለሚሰማሩ የጤና ባለሙያዎች አልባሳትን ማምረት ጀመረ

168

ባህር ዳር ፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ህክምና ለሚሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የሚያገለግል ደረጃውን የጠበቀ አልባሳት ማምረት መጀመሩን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በእውቀትና ግብዓት በማቅረብ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።

በተለይም ህይወት ለማዳን ህይወታቸውን ሰጥተው የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት አልባሳት አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩን ለመፍታት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ጤንነታቸው ተጠብቆ ህሙማንን ማገልገል የሚችሉበትን አልባሳት ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

ምርቱን ቅድሚያ ለክልሉ ጤና ባለሙያዎች በማቅረብ በቀጣይ የማምረት አቅሙን በማሳደግ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለማቅረብ መታሰቡንም አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያለውን የእውቀት አቅም በመጠቀም የፊት መሸፈኛ ማስክና የንዕህና መጠበቂያ አልኮል በማምረት ለህብረተሰቡ እያከፋፈለ እንደሚገኝም ገልፀዋል። 

በሃገራችን የተደቀነው የኮሮና ወረርሽኝ እስኪጠፋ የህዝብ ሃብት የሆነው የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ፍሬው አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የህዝብን ችግር ቀድሞ በመረዳት አልባሳቱን በራሱ ተነሳሽነት ማምረት መጀመሩ የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። 

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተመሳሳይ ወቅት በዓለም ላይ የተከሰተ በመሆኑ አልባሳቱን በቀላሉ በገበያ ላይ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነም ተናግረዋል።

“የችግሩን ስፋት በመረዳት በምርምር ታግዞ ለመፍታት የተሄደበት እርቀትና የተገኘው ውጤት የህክምና ባለሙያዎችን ጤንነት ለመጠበቅ እፎይታ የሰጠ ነው”ብለዋል።

ለአልባሳቱ የሚሆኑ ተፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ምርቱ በስፋት ተደራሽ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አበራ ከጪ በበኩላቸው “ለህክምና ባለሙያዎች የተመረተው ልብስ ፈሳሽና አየርን ወደ ውስጥ ማሳለፍ የማይችል ደረጃውን የጠበቀ ነው”ብለዋል።

ልብሱን ማምረት ከመጀመሩ በፊት ከጨርቅ መረጣ ጀምሮ የተለያዩ የላብራቶሪ ደረጃዎች በባለሙያዎች በአግባቡ ተፈትሾ እንዲያልፍ መደረጉን አስረድተዋል።

በቀን 400 አልባሳትን በጥራት በማምረት ከመጭው አርብ ጅምሮ ማሰራጨት እንደሚጀመር ገልጸው “ልብሱን በስፋት አምርቶ ለክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ የጥሬ ዕቃ ግብዓቶችን ከወዲሁ ለማሟላት የሁሉም አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ኢንስቲትዩቱ ከ13 ሺህ በላይ የፊት መሸፈኛ ማስኮችን አምርቶ ለህብረተሰቡ ማሰራጨቱን ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የጤና ባለሙያዎች አልባሳት መጠነኛ ማስተካከያዎችን በማድረግ ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ምክረ ሀሳብ መሰጠቱን የተናገሩት ደግሞ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቆየ ናቸው።

“በተለይም አሁን ላይ ካለው አንገብጋቢ ችግርና የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት አንፃር አልባሳቱን ከውጭ ማስመጣት የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመሆኑ ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ሃሳብ ተሰጥቷል”ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከ7ሺህ 400 በላይ የመኝታ አልጋዎች ያሏቸው የዘንዘልማና ይባብ ካምፓሶችን ለለይቶ ማቆያ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረጉ የሚታወስ ነው።