የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎች እንደ ወረርኝሽኙ ስርጭትና ጉዳት እየታየ እንደሚወሰን መንግስት አስታወቀ

479

መጋቢት 30/2012(ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎች እንደ ወረርኝሽኙ ስርጭትና ጉዳት እየታየ እንደሚወሰን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና በህዝብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ዛሬ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የተሻለ ነፃነት እና አቅም እንዲኖረው፣ የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ገደቦች ወይም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በተለየ ሁኔታ ለጊዜው ተፈፃሚነታቸው ቀርቶ በሙሉ ሀይል፣ በተቀላጠፈና በተቀናጀ መልኩ ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አዋጁ መውጣቱን አብራርተዋል።

የአዋጁ ዓላማም ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ የመደንገግ ስልጣንን ለስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካል ለመስጠት መሆኑን ጠቁመዋል።

አዋጁ ስርጭቱን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንዲሆኑና በህገመንግስታዊ መብቶች ላይ ሊደርሱ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከአስፈላጊው መጠን ያላለፈ እንዲሆን  እንዲሁም እንደ ጊዜውና እንደአካባቢው ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን አብራርተዋል።

የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ማብራሪያ 

መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም 

1.የአዋጁ አስፈላጊነትና ዓላማ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ለአገር እና ለሕዝብ አደጋ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዋጅ የሚተዳደርበትን ስርአት በአንቀጽ 93 ላይ አስቀምጧል። በአንቀጽ 93(1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ ከሚሆኑ ሁኔታዎች አንዱ “የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት” የሚል ነው።

ኮቪድ-19 የሕዝብን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ እንደሆነ እሙን ነው። ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ከተለመደው አሰራር እና ሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፍ ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይጠይቃል።

አዋጁ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የተሻለ ነጻነትና አቅም እንዲኖረው፣ የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ገደቦች ወይም የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በተለየ ሁኔታ ለጊዜው ተፈጻሚነታቸው ቀርቶ በሙሉ ኃይል፣ በተቀላጠፈ እና በተቀናጀ መልኩ ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በማሰብ ይሄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ከሕግ አንጻር አስቻይ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ፣ የዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላማ፣ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ተግዳሮቶችን በተመለከተ አስፈላጊውን እርምጃዎች የመደንገግ ስልጣን ለሥራ አስፈጻሚው የመንግስት አካል መስጠት ነው። እነዚህ ዓላማዎች ያሉት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዛሬው ዕለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።

2.የአዋጁ ይዘት 

የአዋጁ አንኳር ይዘት በአዋጁ አንቀጽ 4(1) የተገለጸው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወረርሽኙ ስርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብአዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስ እና ለመከላከል ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚያወጣቸው ደንቦች የመብት እገዳዎችና እርምጃዎችን በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 93(4) (ሀ) እና (ለ) መሰረት

ለመደንገግ የተሰጠው ስልጣን ነው። ይህም ማለት የወረርሽኙ ሥርጭት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለመከላከል እንደሁኔታው እና እንደአስፈላጊነቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት የመብት እገዳዎችን ማድረግ እና እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል።

እነዚህን የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ከጊዜ ጊዜ እና በአገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው። እንደወረርሽኙ ስርጭት የስፋት አድማስ፣ እንደሚያስከትለው ጉዳት አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ሊለዋወጡ ይችላሉ።

አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልጉት ክልከላዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተለዋዋጭነት ሊኖራቸው ስለሚችል፣ ይህን ከገንዛቤ በማስገባት፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ በመገምገም እና ስለቫይረሱ ስርጭትም ሆነ ባህሪ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን፣ የህዝብ ጤና ባለሙያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝርዝር እና ቋሚ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ (flexible) በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎች እና እርምጃዎች እንዲደነግግ አዋጁ ስልጣን ይሰጠዋል።

አዋጁ በዚህ መልክ የተቀረጸው አስፈላጊ የሆኑ የመብት እገዳዎች እና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ሊለዋወጥ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ፣ ተጨባጭ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ የሆነ እገዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት ነው።

ይህ አይነት አካሄድ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ እና በሕገ-መንግስታዊ መብቶችም ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አስፈላጊ ከሆነው መጠን ያላለፈ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል። በደፈናው ከሚጣሉ ገደቦች ይልቅ፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ እና ስጋት ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲህ ያለ ማዕቀፍ ተመራጭ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማንኛውም ሁኔታ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸው ድንጋጌዎች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ሕግ እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ በተለመደው አሰራር መሰረት ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የ ”አስፈላጊነት” እና “ተመጣጣኝነት” መርሆዎችም የሚኒስትሮች ምክር ቤትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስልጣን የሚገድቡ አጠቃላይ መርሆዎች ተደርገው በታሳቢነት የሚወሰዱ ናቸው።

•አዋጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከተ የመብት እገዳዎቹና እርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለእዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ያመለክታል።

•አዋጁ ማንኛውም ሰው በእዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በህግ ስልጣን ባለው አካል የሚሰጥ ሕጋዊ ትዕዛዝ እና መመሪያን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማት እና ሌሎች በሕግ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም በአዋጁ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ይፋ የተደረጉ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን የማስፈጸም ስልጣን እንደሚኖራቸው ይደነግጋል።

•አንቀጽ 6 በወንጀል ሕግ የተካተቱ አግባብነት ያላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ1 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መዋጮ ሊቀጣ እንደሚችል ያስቀምጣል።

•አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 7 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የሚደነገጉ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እና ሕግ የማስረጽ ኃላፊነት በተጣለበት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በስፋት ለሕዝብ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሀን መግለጽ እንዳለባቸው ይደነግጋል። የፌደራልም ሆነ የክልል፣ እንዲሁም የግል ሚዲያዎች ከዚህ ጋር የሚሰጡ ማብራሪያ እና ገለጻዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለህዝብ የማድረስ ኃላፊነት እና ገዴታ አለባቸው።

•አዋጁ በመላው ሃገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል።