የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ከነገ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

64

ሀረር ፣ መጋቢት 30 /2012 (ኢዜአ) በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ከነገ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ ።

የዩኒቨርሲቲው የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለምሸት  ተሾመ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ ምርመራ ስራውን የሚጀምረው ሐረር ከተማ በሚገኘው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ ነው።

በኮሌጁ የህጻናት ጤናና ሞት ክትትል ፕሮጀክት ቤተ ሙከራ ውስጥ የሚያከናወነው የኮሮና ቫይረስ የመመርመሪያ መሳሪያ ሙሉ ለሙሉ አውቶማቲክ ተደርጎ ከተሰራ በቀን 1 ሺህ 800 ናሙናዎችን በከፊል ከሆነ ደግሞ 600 ናሙናዎችን መመርመር የሚችል ነው ብለዋል ።

ቤተ ሙከራው በተለይ ከምስራቁ የአገሪቱ አካባቢ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚላኩለትን ናሙናዎች መርምሮ  ውጤቱን በፍጥነት ለማሳወቅ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩኒቨርሲቲው ከቫይረሱ ጋር  በተያያዘ በሚያከናው ነው  የመከላከል ስራም እስከ አሁን ድረስ 283  ሊትር ፈሳሽ  ሳሙናና  ሳኒታይዘር  በአካባቢው ለሚገኘው የአዴሌ ማረሚያ ቤት መስጠቱን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ቫይረሱን ለመከላከል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሁሉም ወረዳዎች ላይ ባለሞያዎችን በመመደብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ ለደደር፣ጋራ ሙለታና ጉርስም ወረዳ ለሚገኙ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እያመረተ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሪክተሩ በቀጣይ ሳምንትም ለአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚያሰራጭ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ዋናው ጊቢ በአንድ ክፍል አንድ ሰው ብቻ የሚይዝ 3 ሺህ 894 የማቆያ ክፍሎችን ማዘጋጀቱን አቶ አለም እሸት አያይዘው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም