በማእከላዊ ጎንደር ገበያን የማረጋጋት ስራ እየተካሔደ ነው

57

ጎንደር ፣መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ለማድረግ 10 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

ፀሐሃይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን ከ15 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለህብረተሰቡ አሰራጭቷል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አይቸው ታረቀኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት የፍጆታ ምርቶች አቅርቦቱ መሰራጨት የጀመረው በ26 ህብረት ስራ ማህበራትና ዩንየኖች አማካኝነት ነው።

ማህብራቱና ዩኒየኖቹ የአቅርቦት ክፍተት ያለባቸውን የግብርና ምርቶችና የፍጆታ እቃዎችን በቀጥታ ከአምራቹ በመረከብ ለተጠቃሚው በማቅረብ ላይ ናቸው ።

በቫይረሱ ሳቢያ አንዳንድ ነጋዴዎች በፍጆታ እቃዎች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ከማድረጋቸውም በላይ የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር ምርቶችን የመደበቅና የማከማቸት ህገ-ወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ ተደርሶባቸዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የማስተካከያ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጎን ለጎን በተመረጡ ወረዳዎች 6 የገበያ ማእከላት በማቋቋም የምርት እቅርቦት እጥረቱ እንዲፈታ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡

በማእከላቱ አርሶ አደሩ የግብርና ምርቶችን ከደላሎችና ከህገ-ወጥ ነጋዴዎች በፀዳ  መልኩ ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በቀጥታ በሽያጭ በማቅረብ ህብረተሰቡ ምርቱን እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የፀሐይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪያጅ አቶ ደረበ አቤ በበኩላቸው የዘይት ምርት አቅርቦትና የዋጋ ንረትን ችግር ለመፍታት ከ15 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ማቅረብ ተችሏል፡፡

ዩንየኑ ነጋዴዎች በ460 ብር ሒሳብ የሚሸጡትን  ባለ 5 ሊትር እሽግ  ዘይት  በ400  ብር  ሂሳብ በመሸጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል ዩንየኑ ቀይ ሰርገኛና ነጭ ጤፍ በኩንታል ከ400 እስከ 500 ብር ቅናሽ በማድረግ 1ሺ 200 ኩንታል ጤፍ በጎንደር ከተማ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች ማሰራጨቱን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ማናሌ ሞገስ በበኩላቸው የኮሮና በሽታ ወሬ ከተሰማ ማግስት ጀምሮ ነጋዴዎች ጭማሪ ያላደረጉበት የፍጆታ ምርት የለም ብለዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ባለ አምስት ሊትር እሸግ የምግብ ዘይት በ400 ብር መግዛታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ማናሌ ዛሬ ግን ከ460 ብር በታች የሚሸጥ ነጋዴ ካለመኖሩም በላይ የዘይት ምርቱ ከገበያ ላይ ጠፍቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከገበያ ዋጋ 60 ብር ቅናሽ ያለውን የምግብ ዘይት ከፀሐይ ዩንየን የመሸጫ ሱቅ መግዛት በመቻላቸው መደሰታቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ብርቱካን ቻላቸው ናቸው፡፡

በዞኑ ወቅታዊ ሁኔታውን በመጠቀም የዋጋ ንረት የፈጠሩና የፍጆታ  ምርቶችን  ያለአግባብ ደብቀው በተገኙ 367 ነጋዴዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም