በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የተከፈተው ዘመቻ ተገቢነት የሌለው ነው - ሙሳ ፋቂ ማሃማት

86

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) ''በዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የተከፈተው ዘመቻ ተገቢነት የሌለው ነው'' ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ገለጹ።

ሊቀመንበሩ የአሜሪካ መንግስት በዓለም የጤና ድርጅት አመራሮች ላይ የከፈተው ዘመቻ እንዳስገረማቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መረጃ አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት የዓለም የጤና ድርጅትና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ሙሉ ለሙሉ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት ትኩረት መደረግ ያለበት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ ሆኖ ኮቪድ-19ን መከላከል እንደሆነና የተጠያቂነት ጉዳይ ወደፊት የሚመጣ ነገር ነው" ብለዋል።

የአሜሪካው የድጋፍ ፊርማ አሰባሳቢ ድረገጽ "ቼንጅ ዶት ኦርግ" የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከስልጣናቸው እንዲነሱ የድጋፍ ፊርማ እያሰባሰበ ይገኛል።

ድረ ገጹ ፊርማ እያሰባሰበ ያለው "ዶክተር ቴድሮስ ቀደም ብለው ኮሮናቫይረስን (ኮቪድ-19) ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ብለው አላወጁም፤ ቫይረሱን ለመከላከል የሰጡት ግምትም አነስተኛ ነው" በሚል ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም