የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎች የአምራቹ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

52

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎች የአምራቹን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያወጣቸው መመሪያዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ በአግባቡ እንዲተገበሩ እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ ህጎች ሊወጡ ይችላሉም ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭትና የመከላከል ሂደትን አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙሃን ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት፤ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያወጣቸው መመሪያዎች የአርሶ አደሩን ብሎም የአምራቹን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

"አምራቾች በተለይም ደግሞ አርሶ አደሮች ካላመረቱ የሚከሰተው ረሃብ ተጨማሪ ችግር ስለሚሆን የሚወጡ መመሪያዎች ይሄን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እያንዳንዱ እንቅሴቃሴ ቢገታ መንግስት በቂ የሆነ ምግብ የማቅረብ አቅም እንደማይኖረው ገልጸዋል።

መርሃችን 'እንጠነቀቃለን፣ እንሰራለን፣ እናመርታለን' ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ "የሚወጡ መመሪያዎች የኅብረተሰቡን የማምረት እንቅስቃሴ አይገድቡም" ብለዋል።

የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ይገደብ ቢባል በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችለው ረሃብ ሌላ ተጨማሪ እልቂት ሊፈጥር እንደሚችልም አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ እንደየአካባቢው ቢለያይም በመንግስት የተላለፉ ውሳኔዎች በኅብረተሰቡ በኩል አተገባበራቸው ልዩነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

"በከተማና በገጠር የኅብረተሰቡ አኗኗር ዘይቤ የተለያየ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ኅብረተሰቡ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ይቀጥላል" ብለዋል።

"መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ያወጣቸው መመሪያዎች በመንግስት ተቋማት የተሻለ ተግባራዊ ተደርገዋል" ያሉት አቶ ንጉሱ፤ በግል ተቋማት ውስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

"በመሆኑም መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ መመሪያዎችን በማውጣት ኅብረተሰቡ ወጥነት ባለው መልኩ እንዲከላከል ይደረጋል" ብለዋል።

የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በቸልታ የሚያልፉ አካላትን ከማስተማር ባለፈ ህግ የማስከበር እርምጃ መንግስት እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

"በዓለም ብሎም በኢትዮጵያ አደጋ ባንዣበበበት ወቅት ለትርፍ የሚሯርጡ አካላት በሞራልም ሆነ በህግ ተጠያቂ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም