በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በ14 ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ ተከሰተ

661

ነገሌ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ)  በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በ14 ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ በመከሰቱ በበልግ አዝመራ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብትና የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሊበን ቦሩ እንደገለፁት በዞኑ 14 ወረዳዎች ለ4ኛ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው የአንበጣ መንጋ ተከስቷል ።

የዞኑን ህዝብ በማስተባበር በባህላዊ ዘዴ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ከአንበጣው መንጋው ብዛት አንፃር ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ባለሙያው ተናግረዋል ።

ችግሩ ተባብሶ በሚታየባቸው በዞኑ ዋደራ ፣ ሊበንና አጋ ዋዩ ወረዳዎች የፌደራል መንግስት በአውሮፕላን ያደረገው የመድሀኒት ርጭትም ቢሆን ቀጣይነት ስለሌለው  ዳግም መከሰቱን ጠቁመዋል፡፡

መንጋውን በጊዜ መከላከል ካልተቻለ በበልግ አዝመራ በዘር በሚሸፈነው ከ60 እስከ 100 ሺህ ሄክታር ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡

የመከላከል ስራው ከዞኑ ህዝብና መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ ለክልሉና ለፌደራል መንግስት ጥያቄ ቀርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ ነን ብለዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በፌደራልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ የሊበን ወረዳ አርሶ አደር አቶ በሩ ዲዳ ሰሞኑን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በተለይ በእንስሳት መኖና በተፈጥሮ ደኖች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡

ድምጽ በማሰማት በባህላዊ መንገድ ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ እንዲሄድ ካልሆነ በስተቀር ማጥፋት እንዳልተቻለ  ጠቁመዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው ያለመንግስት እርዳታና ድጋፍ በባህላዊ መንገድ ብቻ መከላከል ስለማይቻል በበልግ አዝመራ ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል ።

አቶ ስዩም ኩላ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው አንድ ጊዜ መሬት ላይ ካረፈ አረንጓዴ ቅጠል የሚባል ነገር አይታይም ብለዋል፡፡

ብዛቱ ፣ የሚያደርሰው ጉዳትና የበረራ ፍጥነቱ እጅግ በጣም አስፈሪ በመሆኑ የበልግ አዝመራ ከመድረሱ በፊት መንግስት ከወዲሁ መላ እንዲፈለግለት ጠይቀዋል፡፡