ከፒያሳ ወደ ጃንሜዳ የተዛወረው የአትክልት ተራ ግብይት ተጀመረ

111

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ ፒያሳ ይካሄድ የነበረው የአትክልት ግብይት ወደ ጃንሜዳ ተዛውሮ ዛሬ ሥራ ቢጀምርም አነስተኛ የችርቻሮ ነጋዴዎች ግን የግብይት ስፍራው "እኛን ታሳቢ አላደረገም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። 

የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ አካላዊ ጥግግትን ለመቀነስ ሲባል መንግስት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የመንግስት ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎችም የተሳፋሪዎችን ቁጥር እንዲቀንሱ ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ በገበያ ስፍራ በግብይት ወቅት የሰዎችን ጥግግት ለመቀነስ የተጨናነቁ የገበያ ሥፍራዎች ሰፋ ወዳሉ አካባቢዎች እንዲዛወሩ እየተደረገ ነው።

ለዚህም በፒያሳ አትክልት ተራ በጠባብ የግብይት ስፍራ ላይ የነበረው የአትክልት ግብይት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጃን ሜዳ እንዲዛወር ተደርጓል ።

የኢዜአ ሪፖርተር በጃንሜዳ ባደረገው ቅኝት ለህጋዊ ነጋዴዎች የተሰጠውን ቦታ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች ቀድመው ስለያዙት ህጋዊ ነጋደዎቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ ታዝቧል።

በግብይቱም የሸማችና ነጋዴዎች ብዛት አነስተኛ መሆኑን ለማየት ተችሏል።

የአነስተኛ የችርቻሮ ነጋዴዎችም የጃንሜዳ የግብይት ስፍራ"እኛን ታሳቢ አላደረገም፣ መሸጫ ስፍራ አልተሰጠንም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ወይንሸት ከማል የተባሉ አስተያየት ሰጭ "መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የገበያ ስፍራውን ማዘዋወሩ መልካም ቢሆንም በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተን የዕለት ጉርስ ለምናገኝ ሰዎች ፈታኝ በመሆኑ ሁሉንም ያማከለ መፍትሄ ይስጠን ሲሉም" ጠይቀዋል።

በዚህ ሥራ መተዳደር ከጀመረ ከ10 ዓመት በላይ እንደሆነው የገለጸው ወጣት ዮናስ ቅባቱም መንግስት አቅም ያላቸውንና የሌላቸውን ነገዴዎች ግምት ውስጥ ያስገባ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ነው ያለው።  

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል የፒያሳ አትክልት ተራ ገበያ በጊዜያዊነት ወደ ጃንሜዳ እዲዛወር መደረጉን ገልጸዋል።

የገበያ ቦታው የተቀየረው አትክልት ተራ በርካታ ሰዎች የሚገበያዩበት ትልቅ የገበያ ማዕከል በመሆኑ የሰዎችን አካላዊ ጥግግት ለመቀነስ ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በፒያሳ አትክልት ተራ ሲሰሩ ለነበሩ 704 ህጋዊ ነጋዴዎች በጃንሜዳ የመሸጫ ቦታ የማከፋፈል ሥራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

የንግድ ፈቃድ የሌላቸውና በአነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች ግን የኮሮናቫይረስ እስኪወገድ ድረስ አካላዊ ጥግግቱን ለመቀነስ ሲባል በየአካባቢያቸው ሽያጫቸውን ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

ይህ አሰራር ጊዜያዊና ወረርሽኙ እስኪያልፍ ድረስ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መስፍን፣ "ሰርቶ መግባት የሚቻለው ጤና ሲኖር" በማለት ችግሩ እስኪያልፍ የመንግስትን አቅጣጫ መቀበል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር ሰፊ ቅስቀሳ እየተደረገ ቢሆንም በህብረተሰቡ ላይ እየታየ ያለው ለውጥ አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል።

ግንዛቤ የሚፈጥሩ አካላት ህዝብ በሚበዛባቸው የገበያ ሥፍራዎች ላይ ተገኝተው አብረዋቸው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም