የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

88

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።

የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው ድጋፍ መደረጉን ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታውቀዋል።

አቶ ኢየሱስወርቅ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ለአገራቸው ልማት ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው።

ነገር ግን አሁን የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በአስቸኳይ ድጋፍ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ እንደወሰኑ ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ መንግስት ችግሩን ለመከላከል በሚመርጠው መንገድ በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት ለማበርከት ዝግጁነት እንዳለ ጠቁመዋል።

ትረስት ፈንዱ በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ገቢ ማሰባሰቢያ ዌብሳይት መከፈቱን አቶ ኢየሱስወርቅ ገልጸዋል።

እርሳቸውም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን የ5 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዌብሳይቱ የሚሰባሰበው ድጋፍ ቀስ በቀስ እያደገ ትርጉም ያለው ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይም ሰባት የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚገልጽ ደረሰኝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ተገኝተው ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክበዋል።

ድጋፉን ያደረጉት ሰባት የተለያዩ ድርጅቶች መሆናቸውም ታውቋል።

ቮለንታሪ ሰርቪስ ኦርጋናይዜሽን፣ ተስፋ ድርጅት፣ ራስአገዝ የሴቶች ድርጅት፣ፓዝፋይንደር፣ ኦርጋናይዜሽን ፎር ዌልፌር ኤንድ ደቨሎፕመንት፣ የአማራ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት እና እነሆ ፍቅር ሂዩማኒታሪያን የልማት ድርጅት የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ድጋፍ መደረጉን የሚገልጸውን ደረሰኝ የተረከቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ካላቸው በመለገስ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በትብብር ለመከላከል ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሽታውን ለመከላከል እየተረባረበ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ''የእኛ ትልቁ አቅም በሽታውን ማከም ሳይሆን መከላከል ነው'' በማለት ህብረተሰቡ ተገቢውን የጥንቃቄ ርምጃ እንዲወስድ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም