የአንበጣ መንጋ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ላይ ጉዳት አድርሷል

105

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የበርሃ አንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ወራት ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመከላከል ስራዎችን በኮረኖናቫይረስ ምክንያት ከሰው ኅይል ይልቅ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የማድረግ ተግባራት ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ዛሬ በሰጡበት መግለጫ፤ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ በግብርና ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት መገለጹ ይታወሳል።

በመሆኑም በምስራቅ ኢትዮጵያ ጀምሮ ወደ ሰሜንና ደቡብ ኢትዮጵያ የተስፋፋው የአንበጣ መንጋ እስካሁንም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አለመጥፋቱን ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋው ካልተቆጣጥርነው በቀጣይም በምርት መጠን ላይ መቀነስ እንደሚያደርስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት በተደረገ የመጀመሩያ ዙር ጥናት የአንበጣ መንጋው ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ላይ ጉዳት አድርሷል።

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ የአንበጠጣ መንጋው መስፋፋት እስከ ቀጣዩ ነሃሴ ወር ሊቀጥል ይችላል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሰው ሃይል ለመከላከል ሲደረግ የነበረውን ጥረት ስለሚያስተጓጉለው በቴክኖሎጂ የመከላከል ስራ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በሄሌኮፕተር ታግዞ ለሚደረግ መከላከል ስራም ከደቡብ አፍሪካ ሄሌኮፕተሮችን ለማስመጣት ስምምት ቢደረግም ሄሌኮፕተሮቹ ሶስት አገራትን አቋርጠው ስለሚገቡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በየአገራቱ ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ መቆም እንደሚገደዱ ገልጸዋል።

በዚህም ለጊዜው ጉዳዩን በመሰረዝ በአገር ውስጥ የግል ሄሌኮፕተሮች በመታገዝ የመከላከል ስራው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ችግሩን ለመከላከል ድሮንና ሄሌኮፕተር መጠቀም የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ትኩረት ይደረግበታል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት ኬምቴክስ ከተባለ በእርሻ ግብዓቶች አስመጭ የግል ድርጅት ለአንበጣ መከላከያ የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በድጋፍ አግኝቷል።

የደርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ይመኑ ጀምበሬ ድርጅታቸው ለአንበጣ መንጋ መከላከያ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 400 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድርጉን ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን የድርጅቱን ድጋፍ በመቀበል ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም