ለዘላቂ ልማት ግቦች ውጤታማነት የኮሮናቫይረስን ጨምሮ ሌሎች ፈተናዎችን በጠንካራ ትብብር ማለፍ ወሳኝ ነው

80

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ የኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ-19) ጨምሮ ሌሎች ፈተናዎችን በጠንካራ ትብብር ማለፍ እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አስታወቀ።

የዘላቂ ልማት ግቦች የአፍሪካ ቀጠና መድረክ ቢሮ (ኤ አር ኤፍ ኤስ ዲ) ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በዚህም የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ እየሰፋ መምጣቱንና እያደረሰ ባለው ጉዳትና በጋረጠው ፈተና ላይ አተኩሮ ተወያይቷል።

"በቫይረሱ ምክንያት በአፍሪካ እየጨመረ የመጣው የሟቾች ቁጥርና በማህበራዊም ሆነ  ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያስከተለ ያለው ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦኛል" ሲል ቢሮው አመልክቷል።

አፍሪካ በተለያዩ መስኮች ባሏት ተጋላጭነቶች በቫይረሱ ከፍተኛ ተጎጂ ልትሆን እንደምትችል ነው ያስታወቀው።

የአፍሪካ ህብረት አባል አገራትም አስቸኳይና የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መግታት እንደሚገባቸው ገልጿል።

በተጨማሪም የህብረቱ አባል አገራት በቫይረሱ ምክንያት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መደገፍና በቫይረሱ ምክንያት ለሚመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባቸው ጠቅሷል።

በውይያቱ ላይ ኮቪድ-19 የፈጠራቸውን አስቸጋሪ ፈተናዎች ለማለፍ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዘላቂ የልማት ግቦች ሙሉ ለሙሉ እንዲሳኩ ከተፈለገ ኮሮናቫይረስን ጨምሮ ሌሎች የጤና፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የከባቢ አየር ክስተቶች የሚያደርሱትን የከፋ ጉዳት መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም በውይይቱ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነው።

ለዚህም ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል።

የዘላቂ ልማት ግቦች የአፍሪካ ቀጠና መድረክ ቢሮ የወቅቱ ሊቀ መንበር ዚምባቡዌ ናት፡፡

በውይይቱ በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ቢሮው በዚምባቡዌ ባደረገው ስብሰባ ከስምምነት ላይ የደረሰበትን የ10 ዓመት የድርጊት መርሐግብር አጽድቋል።

የ10 ዓመት የድርጊት መርሐግብሩ ድህነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እኩልነትን ማስፈን፣ ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና ለሌሎች ፈተናዎች ዘላቂ የሆኑ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

መርሐግብሩ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና በተመድ በተዘረጉ የልማት ስርአቶች ተግባራዊ እንደሚደረግና ከ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችና ከአጀንዳ 2063 ጋር ተጣምሮ እንደሚተገበርም ተገልጿል።

ለዚህም ጥራቱን የጠበቀ የተቀናጀ የመረጃ ስርአት ይዘረጋል፤ አስፈላጊው ቁጥጥርም ይደረጋል ተብሏል።

የዘላቂ ልማት ግቦች የአፍሪካ ቀጠና መድረክ ቢሮ አባል አገሮች ዚምባቡዌ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳ፣ ላይቤሪያና ሞሮኮ በስድተኛው መደበኛ ስብስባ አቅጣጫ የተቀመጠባቸው ጉዳዮችን ለመተግበር ቁርጠኛ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ቢሮውም የዘላቂ ልማት ግቦቹ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የአፍሪካ አገራትንና የተቋማትን አቅም የመገንባት ሥራ እንደሚሰራ ማስታወቁን የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል።

የዘላቂ ልማት ግቦች የአፍሪካ ቀጠና መድረክ ቢሮ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ጋር በመተባባር የተቋቋመ የበይነ መንግስታት መድረክ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም