የገቢዎች ሚኒስቴር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር አዋለ

58

መጋቢት 29/2012 ኢዜአ የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሰባት ቀናት ብቻ ግምታቸው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
የተለያዩ ዓይነት አልባሳት፣ ጥራቱ ያልተረጋገጠ የምግብ ዘይት፣ ቡና፣ ስኳር፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎች እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በሀሰተኛ ሰንድ ጭምር በህገ-ወጥ መንገድ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።


በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በዓለም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመቆጣጠር አገራት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።

ቫይረሱ የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋና በአገራት ኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳደረ ባለበት ወቅት የተወሰኑ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ ንግድ መሰማራት ላይ መጠመዳቸው አሳዛኝ መሆኑን የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።

"የሚቀድመው ህዝብን እና አገርን ከወረርሽኙ መከላከልና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን መደገፍ ነው" ብሏል ሚኒስቴሩ።

ይህንን በጎ ሥራ መስራት እየተቻለ ግለሰቦቹ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ገቢ በማጭበርበር፣ በህገ-ወጥ ንግድና በኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በማስገባትና በማስወጣት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ኮንትሮባንድንና ህገወጥ ተግባርን ለመከላከል የተሰማሩ የጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም አጋር አካላት በሚፈጠርባቸው ጫና ሳይበገሩ በትጋት እየሰሩ እንደሚገኝም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

ይህን ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከል ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም አጋር አካላት ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ምስጋና እያቀረበ በቀጣይ ራሳቸውን ከወረርሽኙ መጠበቅ በሚያስችል መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም