በኮምቦልቻ ከተማ አምስት ሆቴሎች ለለይቶ ማቆያ ተሰጡ

54

ደሴ፤ መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) በኮምቦልቻ ከተማ አምስት ባለሃብቶች ሆቴሎቻቸውን በኮሮና ለሚጠረጠሩ ሰዎች ለይቶ ማቆያ እንዲውል በጊዜያዊነት መለገሳቸውን የከተማው ጤና ጥበቃ ጽህፈት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማው የኢንዱስተሪ መንደር ያለበት በመሆኑ የውጭ ሃገራት የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ይበዙበታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኮሮና ቫረስ እንዳይከሰት ቀድሞ የመከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ ለመቆጣጠር እንዲቻል ሁለንተናዊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ባለሃብቶች አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው እስካሁንም አምስት ባለሃብቶች ሆቴሎቻቸውን ለለይቶ ማቆያ መፍቀዳቸውን ተናግረዋል።

ሆቴሎቹ ከ70 በላይ የማረፊያ አልጋዎች እንዳሏቸውና አስፈላጊው ቁሳቁስ የተሟላላቸው መሆኑንም ገልፀዋል ።

ከሆቴሎች በተጨማሪም ሌሎች ባለሃብቶች ለአቅመ ደካሞች የሚውል 60 ኩንታል ዱቄት፣ 780 ሊትር ዘይት፣  200 ብርድ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችንም  ድጋፍ በማድረግ ለወገን ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ ነው።

ባለሃብቶች በሽታውን ለመከላከል እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚደነቅና የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ከባለሃብቶች መካከል ሐጅ አረቡ ኡስማን በሰጡት አስተያየት በሽታውን ለየብቻ በመጓዝ ማሸነፍ የማይቻል በመሆኑ መተባበርና መደጋገፍ ይገባል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ 20 መኝታ ክፍል ያለው ባለ አራት ወለል ህንጻ ለለይቶ ማቆያ እንዲውል ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡

በህንጻው ያሉ የንግድ ክፍሎችንና ካፍቴሪያን ጨምሮ በወር 149 ሺህ ብር ገቢ ያስገኝ እንደነበረ ጠቁመው "ከገንዘብ የሰው ህይወት ስለሚበልጥብኝ ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡

ህዝብ ካለ ገንዘቡ ቀስ ብሎ ይመጣል ያሉት ሐጅ አረቡ ሁሉም የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ ይህን ጭንቅ ቀን ተባብሮ ማለፍ እንደሚገባ አንስተዋል።

አቶ እንድሪስ ይማም የተባሉ ሌላው  ባለሃብት በበኩላቸው ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የኮሮና ቫረስ ለመከላከል ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን መደገፍ ይገባል ብለዋል።

እርሳቸውም 22 የመኝታ አልጋ ያለው ባለ አራት ወለል  ሆቴላቸውን ለለይቶ ማቆያ እንዲውል መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

ከማንኛውም ጥቅም በፊት የሰው ህይወት ይቀድማል ያሉት አቶ እንድሪስ በሽታው ከመስፋፋቱ በፊት የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴም ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡም ከመንግስትና ከሐይማኖት አባቶች የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመተግበር ራሱንና ወገኑን ከቫይረሱ መጠበቅ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ መደጋገፍና መተባበር አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም