የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በቀን 30 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እያመረተ ነው

101

መጋቢት 29/2012 ኢዜአ የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በቀን 30 ሺህ ሊትር የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) እያመረተ መሆኑን አስታወቀ።

የግብአት እጥረት በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት እንቅፋት እንደሆነበትም ገልጿል።

የፋብሪካው ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የማምረት ትኩረቱን በእጅ ንጽህና መጠበቂያ ላይ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅትም በቀን 30 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር በማምረት ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅትና ለተለያዩ ድርጅቶች እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ፋብሪካው የማምረት አቅሙን 50 በመቶ ያህሉን ብቻ በመሆኑ የደንበኞችን ፍላጎት ማሟላት እንዳልቻለ አብራርተዋል።

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ፍላጎት በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ 60 በመቶ የሚሆነውን ፍላጎት ለማሟላት አልተቻለም።

ለምርት ግብአት የሚውል አልኮልና የጠርሙስ እጥረት ድርጅቱ ያለውን አቅም ተጠቅሞ እንዳያመርት ካደረጉት ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሩን በመፍታት ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውለውን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ በቀጣይነት ለማምረት ዕቅድ መያዙንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ከ100 በላይ የተለያዩ መድኃኒቶችን ያመርታል።

"ይሁንና ድርጅቱ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ማምረት ከጀመረ ወዲህ ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ የተወሰኑ የመድኃኒት ዓይነቶችን ማምረት ለማቆም ተገዷል" ብለዋል።

ለኮሮናቫይረስ ማስታገሻና ለሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች የሚውሉ መድኃኒቶች ግን እየተመረቱ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የኮሮናቫይረስ  በኢትዮጵያ ከመከሰቱ በፊትም የግብአትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት አድርጎት መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ሳኒታይዘር ከኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በተጨማሪ በአለርት ሆስፒታል፣ በኢትዮጵያ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እንዲሁም በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተመረተ ይገኛል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እጅን በሳሙና እና በውሃ በደንብ መታጠብ፣ ሳኒታይዘርና አልኮል መጠቀም በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም