የአርባምንጭ እግር ኳስ ክለብ በደደቢት ተጫዋቾች ላይ ያቀረበው የተገቢነት ክስ ውድቅ ተደርጎበታል

58
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደደቢት ተጫዋቾች ላይ ያቀረበው የተገቢነት ክስ ውድቅ ተደረገ። ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት አርባምንጭ ከተማን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ለደደቢት የተሰለፉት ስዩም ተስፋዬና አቤል ያለው በጨዋታው ላይ አምስት ቢጫ እያለባቸው መሰለፋቸው የስነ ምግባር ደንብ የሚጥስ በመሆኑ ክለባቸው ለፌደሬሽኑ የተገቢነት ክስ እንዳለ የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አቅርቦ ነበር። ሁለቱ ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ አምስት ቢጫ በማግኘታቸው መሰለፍ እንደሌለባቸውና ቅጣታቸውን በወቅቱ ለፌዴሬሽኑ አለመክፈላቸውን የሚያሳይ መረጃም ክለቡ አለኝ ማለቱም ይታወሳል። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የተጫዋቾቹን ተገቢነት በማጣራት የተመዘገበውን ውጤት መቀየር እንዳለበት አርባምንጭ እግር ኳስ ክለብ አስታውቆ ነበር። ጉዳዩን ሲያጣራ የነበረው የስነ ምግባር ኮሚቴ ጉዳዩን አቤል ያለው ያየው ቢጫ ካርድ አምስት እንዳልሞላና ሥዩም ተስፋዬ ደግሞ የነበረበት የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ተግባራዊ በመደረጉ እና ያለበትንም የቅጣት ክፍያውን መክፍሉን አስታውቋል። በዚህም ምክንያት አርባምንጭ ከተማ ያቀረበው የተገቢነት ክስ ውድቅ መደረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። ክሱ ውድቅ በመደረጉ ምክንያት የደደቢት ውጤት ባለበት እንዲጸና ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም