በድሬዳዋ በየቀበሌው የሙቀት መጠን የመለካት ዘመቻ ሊጀመር ነው

81

ድሬዳዋ/ኢዜአ/ መጋቢት 29/2012 በድሬዳዋ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በቀበሌ ደረጃ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የሙቀት መጠን መለካት ዘመቻ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን የከተማዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከተከለከለው የህዝብ ትራንስፖርት ውጪ ከከተማዋ የሚወጡና የሚገቡ አሸከርካሪዎች ሙቀት የመለካትና ቫይረስን የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

በተለይ ይህን ሥራ በጤና ቢሮው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የሙቀት መጠን የመለካት ስራ በቀበሌዎች ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

ለዚህ ስራ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች የተሟሉ ሲሆን ሥራው የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ግለሰቦች የመኖሪያ  መንደሮች የሚጀምርና ሁሉንም ቀበሌዎች የሚያዳርስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለሙቀት መለኪያ ፤ ለለይቶ ማቆያ ፣ለመከታተያውና ለህክምና መስጫ ማዕከላት ለሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር መሟላቱንም ወይዘሮ ለምለም ገልፀዋል ፡፡

ቀደም ሲል የኮሮና ቫይረስ ናሙና ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ ይላክ የነበረው ሂደት በማስቀረት በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል ።

ይህም የመከላሉን ሥራ የሚያቃልልና የምርመራ ውጤቶችን ተከትሎ የተቀናጀና ፈጣን የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል፡፡

በአሁን ሰዓት ቫይረስ ከተገኘባቸው ሁለት ሰዎች ጋር ንክኪ የፈጠሩ 36 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያና መከታተያ ገብተዋል፡፡

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምሸት ተሾመ ለኢዜአ እንደተናገሩት የመርመር ስራው ለማስጀመር ለባለሙያዎች አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ከፌደራል ጤና ሚኒስቴርና ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመጡ ባለሙያዎች በመሳሪያዎች አጠቃቀም ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም