በእግር ብቻ የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ ለአገልግሎት በቃ

305

ድሬዳዋ/መጋቢት/ 29/2012 በድሬዳዋ ከተማ አንድ ጎልማሳ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በእግር ብቻ የሚሰራና ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ ሰርቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ አደረገ ።
የፈጠራ ውጤቱ የከተማው ነዋሪ እጁን የመታጠብ ፍላጎቱ እንዲያጎለብትና ወጣቱን ለሌላ ፈጠራ ለማነሳሳት ያግዛል ተብሏል፡፡

ጎልማሳው አቶ ሰለሞን ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለፁት በእግር ብቻ ውሃንና ሣሙናን በመጠቀም ለመታጠብ የሚያስችል የፈጠራ ውጤት የሰራሁት ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ እራሱን እንዲጠብቅ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ብለዋል ።

የፈጠራ ውጤቱ በተለይ ህዝብ በብዛት በሚገለገልባቸው ተቋማትና ሆቴሎች የበለጠ የሚጠቅምና የውሃ ብክነትን ጭምር እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡

የፈጠራ ውጤቱን ለመጠቀም በርካታ ተቋማት ጥያቄ በማቅረባቸው ብብዛት እያመረቱ መሆናቸውንም አቶ ሰለሞን ገልፀዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ለኢዜአ እንደተናገሩት ይህንና ሌሎች ተመሳሳይ የፈጠራ ውጤቶች በተቋማትና ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ።

የፈጠራ ውጤቶቹን መጠቀም ወጣቶቹን ለሌላ ስራ ለማነሳሳት ከማገዙ በተጨማሪ ነዋሪው እጁን የመታጠብ ባህሉ እንዲጎለብት እገዛ ያደርጋል ብለዋል ።

የፈጠራ ውጤት በሆነው መሳሪያ እጃቸውን ሲታጠቡ የነበሩት አቶ ሙክታር እድሪስ በሰጡት አስተያየት  ብዙውን ጊዜ አንዱ በታጠበበት ሳሙና ቀጣዩ ሰው ለመታጠብ ሲያቅማማ እንደሚስተዋል ገልፀው የፈጠራ ውጤቱ ግን ከንክኪ ነፃና ለመታጠብ የሚጋብዝ መሆኑን ተናግረዋል ።