የኢኮኖሚ ትስስሩ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል

323

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የኢኮኖሚ ትስስሩ በኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መቀመጫውን በአቡዳቢ ካደረገው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና ተቋም “አል አይን ኒውስ” ጋር ሁለቱ አገራት ያላቸውን ግንኙነት አስመልክቶ ቆይታ አድርገዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ የለውጥ ስራዎች ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት መካከል በዋነኛነት የምትጠቀስ አገር እንደሆነች ነው የተናገሩት።

የኢኮኖሚ ትብብሩ እያደገ የመጣውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግንኙነት ወደ ሌላ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተለያዩ መስኮች ያላቸው ግንኙነት እያደገ የመጣ ሲሆን በተለይም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የጠነከረ ግንኙነት አላቸው።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአገራቱ መሪዎች በየአገራቱ ያደረጓቸው የሥራ ጉብኝቶች የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉት ጉብኝት የዚህ ማሳያ ነው።

በጉብኝቱ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መብትና ጥቅምን በማስከበር ከተገኙ ውጤቶች በተጨማሪ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጎባቸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ አገራቱ የ3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።