የአፍሪካን የንግድና የፈጠራ ሰዎች የሚያበረታታው የጃክማ ፋውንዴሽን ውድድር ተጀመረ

274

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) በጃክማ ፋውንዴሽን መሪነት የሚካሄደው “የአፍሪካ ኔትፕረነር ሽልማት ተቋም” 2ኛ ዙር የአፍሪካን የንግድ እና የፈጠራ ጀግኖች የመፈለግ እና የማበረታታት ውድድር ተጀምሯል።


የጃክማ ፋውንዴሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በአፍሪካ የማኅበረሰባቸውን ችግሮች ለመፍታት እና የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ለማሳደግ ለሚጥሩ የፈጠራ ሐሳብ ባለቤቶችን የሚደግፈው ውድድር መጀመሩን አስታውቋል። 

ውድድሩ በመላው አፍሪካ የሚገኙ የፈጠራ ባለቤቶችን የማበረታታት እና አቅማቸውን የማሳደግ እንዲሁም ለሌሎች የፈጠራ ባለቤቶች አርአያ በመሆን ተነሣሽነትን እንዲፈጥሩ ማስቻል ዓላማው ያደረገ መሆኑንም አብራርቷል።

በዚህ ውድድር ብርቱ እና ትጉህ ለሆኑ ወደ መጨረሻው ዙር ላለፉ 10 አፍሪካውያን የንግድ እና የፈጠራ ሐሳብ ጀግኖች የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ይጠብቃቸዋል።

ተወዳዳሪዎች ሥራዎቻቸውን ለማሳወቅ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚችሉ የዝግጅት ክፍሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ውድድሩ የዕድሜ እና የጾታ ገደብ የሌለው በመሆኑ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

በ2011ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከ50 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች ማመልከቻ አስገብተው ነበር።

በውድድሩ ወደ መጨረሻው ዙር ያለፉ 10 ተወዳዳሪዎች የንግድ ሐሳቦቻቸውን በጋናዋ ዋና ከተማ አክራ በተካሄደ ዝግጅት አቅርበዋል።

በቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭት በተላለፈው ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች  በዳኞች ፊት ስራቸውን አቅርበዋል።

ተወዳዳሪዎቹ ከንግድ፣ ከግብርና፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከምግብ፣ ከጤና፣ ከውኃ እና መሰል ዘርፎች የተውጣጡም ነበሩ።

በአሊባባ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋም መሥራች አማካኝነት በ2006 ዓ.ም ህዳር ወር መጨረሻ ላይ የተመሠረተው ጃክ ማ ፋውንዴሽን በትምህርት፣ ሥራ ፈጠራ፣ የሴቶችን አቅም በማበልጸግ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና መሰል የበጎ አድራጎት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰማራ የበጎ አድራጎት ተቋም ነው።