የኢጋድ ሠራተኞች ለአባል አገሮች የኮሮናቫይረስ መከላከያ የ700 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ

69

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሠራተኞች ለአባል አገሮች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ የሚሆን የ700 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ።

ሠራተኞቹ ያደረጉት ድጋፍ ለሰባቱ የኢጋድ አባል አገሮች ለእያንዳንዳቸው 100 ሺህ ዶላር እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በስልክ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢጋድ ሠራተኞች ከደመወዛቸው በመቀነስ ለአባል አገሮች ያደረጉት ድጋፍ የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተካፍሎ መብላት አስፈላጊ ነው'' ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ የኮሮናቫይረስ በቀጣናው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ኢጋድ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ኢጋድ የማስተባበር ሥራ በመስራት ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ዶክተር ወርቅነህ ጠቅሰዋል።

ድጋፍ የማሰባሰቡ ስራ በዋና ፀሃፊው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አነሳሽነት የተከናወነ መሆኑም ታውቋል።

የኢጋድ ተወካዮች ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመገኘት ድጋፉን ለኮቪድ -19 ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክበዋል።

በሠራተኞቹ ድጋፍ የተደረገው ገንዘብ ጅቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ 3 ሚሊዮን 291 ሺህ 300 ብር ገቢ ተደርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ህብረተሰቡ ለቫይረሱ ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም