ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ሶፊያ የተሰኘችውን ሮቦት አነጋገሩ

142
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሶፊያ የተሰኘችውን ሮቦት በጽህፈት ቤታቸው አነጋገሩ። እንግሊዘኛ ተናጋሪዋ ሮቦቷ ዛሬ ጥቂት የአማርኛ ቃላቶችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተለዋውጣለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉትም የሶፊያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና አማርኛ ቋንቋን መሞከር አገሪቱን ከቴክኖሎጂው ዘመን ጋር የሚያቀራርብ ነው። የሮቦቷ ስራ ከ60 በመቶ በላይ በኢትዮጵያዊያን እንደተሰራ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ኢትዮጵያዊያን ዕድሉን ካገኙ ብዙ መስራት እንደሚችሉ የሚሳይ ነው ብለዋል። ዕድሉን በመጠቀምም የሚመለከታቸው አካላት ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በዘርፉ ለማሰማራት ማሰብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ሶፊያ የተሰኘችው የሰው የፊት ገጽታ ያላትና የሰው ስሜት በመረዳት ከሰው ጋር መነጋገር የምትችል ሮቦት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2013 መሰራቷ ይታወቃል። ይህቺው ሮቦት በሰሞኑ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የአይ ሲ ቲ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በኢትዮ-ቴሌኮም ስፖንሰር አድራጊነት በኢትዮጵያ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም