የኮሮና ተህዋሲ ክትባት "አፍሪካ ላይ ይሞከር" መባሉን የአለም የጤና ድርጅት አወገዘ

59

መጋቢት 29/2012 የአለም የጤና ድርጅት የኮሮና ተህዋሲ ክትባት "በአፍሪካዊያን ላይ ይሞከር" መባሉን በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የፈረንሳይ ተመራማሪዎች የኮሮና ተህዋሲ ክትባት በአፍሪካ ይሞከር ማለታቸውን አሳፋሪ ብለውታል።

ባለፈው ሳምንት የተህዋሲው ክትባት በአፍሪካ ይሞከር የሚል ሃሳብ በተወሰኑ ተመራማሪዎች መነሳቱ የተሳሳተና አብሮነትን የሚሸረሽር ነው ሲሉ  ዋና ዳሬክተሩ  በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አፍሪካ የማንኛውም ክትባት መሞከሪያ እንደማትሆንና ልትሆንም እንደማትችል ዋና ዳይሬክተሩ በአጽኖት ተናግረዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተመራማሪዎች ይህን መሰል ሃሳብ መስማት አሳፋሪና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ዘመን መነሳት የሌለበትና መቆም ያለበት ሐሳብ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቴድሮስ፣ የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይም የአህጉር ልዩነት ሳይደረግ ለውጤታማነቱ የአለም ጤና ድርጅት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

ለተህዋሲው የሚደረጉ የክትባት ሙከራዎች ህግና ስርአትን ተከትለው እንደሚከናወኑ አረጋግጠዋል።

በቀጣይ የሚደረጉ የክትባት ሙከራዎችም በአፍሪካ፣ አውሮፓ ወይንም በሌሎች የአለም ክፍሎች ክትባቱን ለመሞከር በወጡ አግባቦች ይፈፀማል ብለዋል።

የአለምን ህዝብ ከበሽታው ለማዳን፣ የክትባቱ ፈዋሽነት  በተቀመጡ አሰራሮች መሰረት ከተረጋገጠ በኋላ  በሁሉም የአለም ክፍል እኩል ተግባራዊ ይሆናልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

በመሆኑም "እንደዚህ አይነት የዘረኝነት ሃሳቦችን የአለም ጤና ድርጅት በጥብቅ ያወግዛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት ሁለት የፈረንሳይ ተመራማሪዎች የኮሮና ተህዋሲ ክትባት "በአፍሪካ ይሞከር" ማለታቸው በርካቶችን በማስቆጣት አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም