በቦረና ዞን በዘንድሮው በልግ 92 ሚሊዮን ችግኝ እየተተከለ ነው

144

ነገሌ ኢዜአ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓም አርብቶ አደሩ አካባቢ አረንጓዴ ልማትን በማስፋፋት የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በቦረና ዞን በዘንድሮው የበልግ 92 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ስራ ተጀመረ ።
የቦረና ዞን አርብቶ አደር አካባቢ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ በቀለ ሰቦቃ እንደገለፁት አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል ጎን ለጎን የድርቅ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ በዘንድሮው በልግ 92 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው ።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋት 92 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ የተዘጋጀ ሲሆን እስከ አሁን ድረስም 5 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን አቶ በቀለ ተናግረዋል ።

በዞኑ የበጋ ወራት በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ችግኝ የሚተከልበት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጉድጓድ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል፡፡

በአርብቶ አደሩ አካባቢ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋትና የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ለተከላ የተዘጋጀው ችግኝ ካለፈው አመት በ20 ሚሊዮን ይበልጣል ብለዋል፡፡

በዞኑ 12 ወረዳዎች በችግኝ ተከላ ስራ 180 ሺህ አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል ።

በዞኑ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋት ከተዘጋጀ 92 ሚሊዮን ቸግኝ ውስጥ የጽድ፣ ኮሶ፣ ዋንዛ ፣ ዝግባ ፣ ግራቪሊያ፣ የእንስሳት መኖና የጥላ ዛፍ የመሳሰሉት ዝርያዎች ይገኙበታል ።

በስራው ሒደት አርብቶ አደሩ ማህበራዊ ርቀቱንና የግልና የአካባቢ ንጽህናውን በመጠበቅ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን እንዲከላከል በ83 በጎ ፈቃደኞች በየቀኑ ትምህርት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

በቦረና ዞን ባለፈው አመት አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋት ከተተከለው 70 ሚሊዮን ችገኝ ውስጥ 62 በመቶ መጽደቁን በባለሙያዎች ምልከታ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡

የያቤሎ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዲዳ ሞሉ በሰጡት አስተያየት መንግስትና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ፣ ትምህርትና የጥንቃቄ መልእክት በመቀበል ማህበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው የጀመሩትን የልማት ስራ አጠናከረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት ያለሙትን የጥላ ዛፍና የእንስሳት መኖ ከተጠቃሚነት አልፎ መጠነኛ የድርቅ ተጋላጭነትን የቀነሰላቸው በመሆኑ ጥቅምና ጉዳቱን ተረድተናል ብለዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሀሱማ ጃተኒ የቦረና ዞን በአብዛኛው ዝናብ አጠርና ለድርቅ የተጋለጠ በመሆኑ አረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል ።

የኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ የጤና ችግር ስጋት ቢሆንም የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የማይቋረጥ በመሆኑ ማህበራዊ ርቀቴን ጠብቄ የጀመርኩትን የችግኝ ተከላ ስራ እቀጥልበታለሁ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም