የኬንያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታወቀ

80

መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) የኬንያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታወቀ።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 158 መድረሱን ተክትሎ የሀገሪቱ መንግስት በናይሮቢ ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች የእንቅስቃሴ ዕገዳ መጣሉን አስታውቋል።

የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሀገሪቱን የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ መንግስት ጠንከር ያሉ የመከላከል ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረትም እ.ኤ.አ. ከዛሬ ምሽት ኤፕሪል 06 ቀን 2020 07:00 AM ጀምሮ ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ ወደ አጎራባች ክልሎች እና ወደ ለሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደረግ ምንም ዓነይት የየብስ፣ የአየር እና የባቡር ጉዞ ታግዷል።

በናይሮቢ ከተማ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎችም የሰዓት ዕላፊ ገደቡን ያከበሩና ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ሊከናውኑ እንደሚገባም ፕሬዚደንት ኡሁሩ አሳስበዋል።

በኬንያ ባህር ዳርቻ ክልሎች በሆኑት ሞምባሳ፣ ክዋሌ እና ኪሊፊም እ.ኤ.አ. ከረቡዕ፣ ኤፕሪል 08 ቀን 2020 07:00 AM ጀምሮ የእንቅስቃሴ ዕገዳው እንደሚተገበር ፕሬዚንደቱ ገልፀዋል።

ኬንያ በኮሮና ቫይረስ መባባስ ሳቢያ በአሳሳቢ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ያሉት ፕሬዚደንት ኡሁሩ እንዳሁኑ የብሔራዊ ጥቅሟን በዚህ ደረጃ ለስጋት የዳረገና የተፈታተናት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደማያውቅ ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት 4ሺህ 272 ሰዎች ተመርምረው 16ቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በኬንያ ያለውን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 158 አድርሶታል።

ጠንካራ ዕርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር አዳጋች መሆኑን መንግስታቸው መረዳቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው ፤መልካም ጊዜ እንዲመጣ ብንፀልይም ለከፋ ሁኔታ መዘጋጀት ይገባናል ብለዋል።

ሕዝቡም የመንግስት መመሪያዎችን አንዲያከብር አሳስበው ዕድሜያቸው ለገፉና ለበሽታ የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ ለሚችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄና እንክብካቤ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በናይሮቢ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲም በኬንያ የሚገኙ  ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ መንግስት የሚደነገጉ መመሪያዎችን በመከታተልና በአግባቡ በመተግበር የራሳችሁን፣ የቤተሰቦቻችሁን ብሎም የወዳጅ ዘመዶቻቸውንና የወገናችውን ሕይወት እንዲታደጉ አሳስበዋል ።

ኤምባሲውን በኬንያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትን በማስተባበር “ይህንን ክፉ ተደጋግፈን እናሳልፈው” በሚል መሪ ቃል የገቢ ማሰባሰብ ስራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

 ስለሆነም በሚከተለው የLIPA na M-PESA PAY BILL ቁጥር በመጠቀም ወገንዎን ይረዱ ዘንድ ሀገራዊ ጥሪውን ዳግም ያቀርባል ።

ምንጭ ፡-በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም