በሃይማኖት አባቶች የታወጀው ጾም፣ ጸሎትና ምህላ ተገቢና ወቅቱን ያገናዘበ ነው - የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) በሃይማኖት አባቶች የታወጀው የጾም፣ ጸሎትና ምህላ መርሃ-ግብር ተገቢና ወቅቱን ያገናዘበ መሆኑን የተለያየ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች ገለጹ፡፡

የኮሮናቫይርስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የሃይማኖት አባቶች ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር ተግባራዊ የሚሆን የጾም፣ ጸሎትና ምህላ ማወጃቸውና ለምዕመናኑ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ኢዜአ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮችን አነጋግሯል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች መካከል ወጣት ሚሊዮን ተስፋዬ፣ የሃይማኖት አባቶች ያስተላለፉት የጾም፣ ጸሎትና ምህላ አዋጅ ተገቢና ወቅቱን ያገናዘብ መሆኑን ገልጿል።

"እንደ ህዝብም አንድ ሆነን ለፈጣሪ ብንጮህ የምንሰማበትን ውሳኔ ነው ያስተላለፉት" ሲል ገልጿል፡፡

ህዝቡ ክርስቲያንና ሙስሊም በሚል ሳይከፋፈል የሃይማኖት አባቶችን ጥሪ በመቀበል፣ በመተጋገዝ፣ በመተባበርና አንድነቱን በማጠናከር የወረርሽኙን ስርጭት መግታት እንዳለበት አመልክቷል፡፡

"ሁላችንም የአባቶችን የጸሎት ጥሪ በመቀበል እንደአገር ለመጣው ቁጣ ከፈጣሪ መልስ ለማግኘት በየሃይማኖታችን ጸሎትና ልመና እናድርግ" ብሏል፡፡

"ጥንቃቄ አንዱ የቁርዓን አስተምህሮት ነው" ያሉት ሼህ አሊ አህመድ አሊ በበኩላቸው ሁሉም በየሃይማኖቱ የአባቶችን የጸሎት ጥሪ በመቀበል በየቤቱ መጸለይ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት ተከታዮች ከመስጊድ እንዲቀሩ የተደረገው የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና የሃይማኖት አባቶች ምዕመናኑ ጸሎቱን በቤት ውስጥ እንዲያደርጉ ያስተላለፉትን ጥሪ በመቀበል መሆኑን ገልጿል፡፡

"አውቆ ገደል እየገቡ አላህ ጠብቀኝ አይሰራም" ያሉት ሼህ አሊ ሁሉም ህብረተሰብ የመንግስትና የሃይማኖት መሪዎችን ጥሪ በመቀበል ለበሽታው ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

"የወረርሽኙን ለመከላከል መንግስት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና የሃማኖት አባቶችም ለአገር አቀፍ ጾም፣ ጸሎትና ምህላ መርሃ-ግብር ጥሪ በማቅረባቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ወይዘሮ እጅጋየሁ ነገራ ገልጸዋል።

በሃይማኖት አባቶች የተላለፈው የአንድ ወር መርሃ-ግብር ጥሪ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ ከቤተ-ዕምነቶች ውጪ ሰዎች የሚያደርጉት ጥግግት እንዲሻሻል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ዘካሪያስ ገብረሚካኤል የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

ለሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች "የአባቶችን የጾም፣ ጸሎትና ምህላ አዋጅ በመቀበል ተግባራዊ እናድርግ፤ በንጹህ ልብ ከለመንን ፈጣሪ ይሰማና፤ ይህንን ክፉ ቀንም እናልፈዋልን" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም