ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን ለማሳደግ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረች-- ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

56

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ  የዲጂታል ኢኮኖሚ  እንቅስቃሴዋን ለማሳደግ የምታከናውነውን ሥራ ፣ ረቂቅ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ በማጽደቅ ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገሯን ጠቅላይ   ሚኒስትር  አቢይ አህመድ ገለጹ።

አዋጁ በፓርላማ ሲጸድቅ፣ በኤሌክትሮኒክ አገልግሎት አማካኝነት የሚፈጸሙ ሁሉንም የግብይት ሂደቶች ለማከናወን የሚቻልበት ደንብ እንዲኖር ያስችላልም ነው ያሉት።

ሕጉ በሁሉም የኮሙኒኬሽን ዘርፎች የሚታየውን የኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፍላጎት መሠረት በማድረግ፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ዲጂታል አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚችሉበትን ግልጽ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

ከሚሰጡት አገልግሎቶች የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና የኤሌክትሮኒክ መንግሥታዊ አገልግሎቶች፣ በኤሌክትሮኒክ ግብይት አማካኝነት ዳታን መለዋወጥ እና ማከማቸት፣ ኤሌክትሮኒክ ምዝገባና ፊርማዎች እንደዚሁም የኤሌክትሮኒክ ዳታ መልእክቶች እንደሚገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የሕጉ መጽደቅ ከንግድ፣ ከቀረጥ፣ ከሰነድ ማረጋገጥ፣ ከማኅተም፣ ከምስክር፣ ከዲጂታል ክፍያ አኳያ ታላቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ገልጸዋል።

የተጠቃሚዎችን መብት ለማስከበርና ዳታ በጥሩ ይዞታ እንዲቆይ ለማድረግም የተሻለ ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ አስቀድመው የተቀመጡትን የሕግ ማሕቀፎች በማይነካ መልኩ፣ ዲጂታል ማስፈጸሚያ ሆኖ በማገልገል፣ በዘመናዊ ኢኮኖሚ አማካኝነት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የሚስችል ቁልፍ ሂደት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም