በትግራይ ደቡባዊ ዞን የአንበጣ መንጋ ተከሰተ

115

ማይጨው፣መጋቢት 28/ 2012 (ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን ራያ አዘቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ገለፀ።

በመመሪያው የአዝርእት  ባለሙያ አቶ ክብሮም በርሀ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው ትናንት አመሻሽ ላይ በራያ አዘቦ ወረዳ በኡራ አባዮና ካራ በሚባሉ ቀበሌዎች መከሰቱን ተናግረዋል።

በአፋር በኩል አድርጎ ወደ ዞኑ የገባው የአንበጣ መንጋ በመስኖ ልማት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የመከላከል ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው እስካሁን ድረስ ጉዳት ባያደርስም  ተጨማሪ መንጋ በአፋር በኩል እየመጣ በመሆኑ  በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የራያ አዘቦ ወረዳ የግብርናና ገጠር ልማት ፅህፈት ቤት ሓላፊ አቶ መልአኩ ግርማይ በበኩላቸው  የአንበጣ መንጋው  ባለፈው የመኸር ወቅት ተከስቶ ከነበረው መንጋ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

መንጋው ትናንት አመሻሽ ላይ በመስኖ ልማት ላይ ለማረፍ ቢሞክርም ህዝቡ በባህላዊ መንገድ  ርችት በመተኮስ እና ጭስ በማጨስ መከላከሉን ተናግረዋል።

መንጋው ባዶ መሬት ላይ ማረፉን ጠቅሰው አሁንም የማባረር ስራው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

መንጋው በሚቀጥለው የመኸር ወቅት  አደጋ ሆኖ እንዳይዘልቅ  ታሳቢ ያደረገ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 የራያ አዘቦ ወረዳ የካራ አዲሻቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሱሌማን ጣሃ በበኩላቸው አርሶ አደሩ  የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እያካሄ ነው ።

ተጨማሪ መንጋ እየመጣ መሆኑን መረጃ እንደተነገራቸው የጠቀሱት አርሶ አደሩ ህዝቡም ነቅቶ እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም