አምስት ሺህ የልማት ተነሺ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

59
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በልማት ተነሺ የሆኑ አምስት ሺህ አባወራ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በዛሬው እለት በከተማዋ የሚገኙትን የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን  በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከንቲባው  በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት አመታት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ብዛት ከመለየት ጀምሮ፤ አርሶ አደሮቹን መልሶ ማቋቋም የሚቻልበትን አቅጣጫ የሚያጠና ጽህፈት ቤት እስከ ማቋቋም የሚደርስ ስራ መሰራቱ ተጠቅሷል፡፡ ባለፉት 26 አመታት በከተማዋ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ብዛት ጥናት ተደርጓል ያሉት ከንቲባ ድሪባ፤ በዚህም ከ6 ሺህ 553 አባወራ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ይህም በቤተሰብ ሲታይ 32ሺህ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ እነዚህን ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በዶሮ እርባታ፣ የከብት ማድለብ ስራ፣ የሆርቲ ካልቸር ልማት፣ አነስተኛ ንግድና ህንጻ ገንብተው ማከራየት የሚችሉበት መንገድ ሲጠና መቆየቱን ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በከተማዋ የሚገኙ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መሰረተ ልማት ከማሟላት ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ስራዎች ይሰራሉ ሲሉ ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በከተማዋ ገላን አካባቢ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አግሮ ኢንዱስትሪ በሶስት ወር ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል፡፡ የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት  ከማረጋገጥ ባለፈ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ይሰራሉ ያሉት ከንቲባ ድሪባ፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 420 ሚሊዮን ብር መበጀቱንም ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ 65 ሄክታር ላይ የከብት ማድለቢያን፣ አምስት የዶሮ እርባታ ማዕከል፣ አምስት የገበያ ማዕከል የተካተቱ መሆናቸውን ከንቲባ ድሪባ  ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአምስት ትምህርት ቤቶችና አምስት መዋዕለ ህጻናት ግንባታም በፕሮጀክቱ እንደ ተካተቱ ተጠቅሷል፡፡ የአግሮ ኢንዱስትሪው እና የመሰረተ ልማት ስራዎቹ በሶስት ወር ይጠናቀቃል ያሉት ከንቲባ ድሪባ፤ በነገው እለትም የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ በይፋ ወደ ግንባታ ይገባል ብለዋል፡፡ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው አግሮ ኢንዱስትሪ ወደ ስራ በሚገባበት ወቅት በከተማዋ  ነዋሪዎች የተለያዩ ምርቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ከንቲባ ድሪባ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከተማ አስተዳደሩ ወደ 52 ሚሊዮን ብር በመመደብ  ለ2 ሺህ 87 አርሶ አደሮች የእለት ምግብና ተያያዥ ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝም ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል፡፡ ወደ 1ሺህ 752 የሚሆኑ መስራት የሚችሉ የአርሶ አደሮች ልጆችም ተደራጅተው በተለያዩ ስራዎች እንዲገቡ በማድረግ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተው፤ ሶስት ሚሊዮን ብር እንዲቆጥቡ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ 5 ሺህ 997 ወደ ስራ ያልገቡ ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ የስድስት ወር ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ እንዲገቡ ምዝገባ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡ ስልጠናቸውን እንደጨረሱም በተለያዩ የግብርና ስራዎች እንዲሰማሩ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም